የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን ከጥፋት መንገድ በመውጣት የሰላምና የልማት ዘብ ለመሆን ተዘጋጅተናል - የቀድሞ ታጣቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን ከጥፋት መንገድ በመውጣት የሰላምና የልማት ዘብ ለመሆን ተዘጋጅተናል - የቀድሞ ታጣቂዎች
ጎሊና፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን ከጥፋት መንገድ በመውጣት የሰላምና ልማት ዘብ ለመሆን ተዘጋጅተናል ሲሉ በአፋር ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎች ገለጹ።
በአፋር ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የቀድሞ ታጣቂዎች፤ በፈንቲ ረሱ ዞን ጎሊና ወረዳ በሚገኘው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የአፋር ጊዜያዊ ዲሞብላይዜሽን ማዕከል ሲከታተሉ የነበረውን የተሃድሶ ሥልጠና አጠናቀዋል።
ከቀድሞ ታጣቂዎቹ መካከል አሰከር ኖራ፤ በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት የአካባቢውን ሕዝብ መበደሉን አስታውሶ በጥፋቱ በመጸጸት ለመካስ መዘጋጀቱን ተናግሯል።
በሥልጠና ቆይታው የልማት አርበኛ እና የሰላም ዘብ ለመሆን ብዙ የተማረበትና ለተግባራዊነቱ ቃል መግባቱን ገልጿል።
ሌሎች በተሳሳተ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችም የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ሰልጥነው ማኅበረሰቡን መቀላቀል እንዳለባቸው አስገንዝቧል።
ሌላኛው የቀድሞ ታጣቂ ከሊል ሙስጠፋ እና መዲና አህመድ፤ በተሳሳተ መንገድ በመመራት እና በመሳተፍ የራስን ወገን ከመበደል በስተቀር የሚመጣ ለውጥ የሌለ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።
በመሆኑም የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ሀገራችንንና ሕዝባችንንም ለማገልገል ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የቀድሞ ታጣቂዎችን በማሰልጠን ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉና መልሰው እንዲቋቋሙ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም መሠረት በአፋር ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል፣ ከስህተታቸው ተምረው የሰላም ኃይልና የልማት አጋዥ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን አንስተው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲገቡ አሳስበዋል።
የአፋር ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አብዱ ሙሳ፤ የቀድሞ ታጣቂዎቹ የሰላም ጥሪን ተቀብለው የተሃድሶ ሥልጠና መውሰዳቸው ለሰላም ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ያሳዩበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም በቀጣይ የሰላምና የልማት አጋሮች ለመሆን መዘጋጀታቸውን ጠቁመው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ድጋፍ እንደማይለያቸው ተናግረዋል።