በድሬዳዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ ናቸው
ድሬዳዋ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሆናቸውን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ገለጹ።
በብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ የምረጡኝ ቅስቀሳ አካል የሆነ አመራሮች፣ የአባላትና ደጋፊዎች የተሳተፉበት የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሂዷል።
በመርሐግብሩ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ እንደገለጹት፤ ስፖርት ጤናማ፣ ተወዳዳሪ እና አሸናፊ ትውልድ ለማፍራት መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ፤ በአስተዳደሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በጥራትና በፍትሐዊነት በገጠርና በከተማ እንዲገነቡ ተደርጓል።
ወጣቶች የነገ ብሩህ ሕይወታቸው ፍሬያማ እንዲሆን በየወረዳው የወጣቶች ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ገልጸዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአስተዳደሩ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፓርቲው የሕዝብን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤታማ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በድሬዳዋ ገጠርና ከተማ ውጤታማ እና ጤናማ ትውልድ ለማፍራት ለስፖርት ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት፣ ተወዳዳሪ ትውልድ በመፍጠር ረገድ ወደር የሌለው ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
በአስተዳደሩ እየተመዘገቡ የሚገኙ ውጤቶችም ሆኑ እንደ ሀገር እየተከናወኑ የሚገኙ አሻጋሪ ፕሮጀክቶች፣ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጉዞ ዕውን የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።