ብሩኖ ፈርናንዴዝ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመረጠ - ኢዜአ አማርኛ
ብሩኖ ፈርናንዴዝ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመረጠ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ የማንቸስተር ዩናይትድ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች (Player of the Season) በመሆን መመረጡን የሊጉ አስተዳደር ይፋ አደረገ።
የፕሪሚየር ሊጉ አስተዳደር እንደገለጸው፣ የ31 ዓመቱ የመሐል ሜዳ ተጫዋች የዓመቱ ምርጥ ተብሎ የተመረጠው በውድድር ዓመቱ ባሳየው የጎል ዕድሎችን የመፍጠር ብቃትና ለቡድኑ ስኬት ላበረከተው አስተዋጽኦ ነው።
ማንቸስተር ዩናይትድ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ በነበረበት የአሰልጣኝ ቅያሬና መዋዠቅ ውስጥ አልፎ በጊዜያዊና በቋሚ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ መሪነት በደረጃ ሰንጠረዡ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ እንዲሁም ወደ አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እንዲመለስ ተጫዋቹ የነበረው ሚና የጎላ እንደነበር ተመላክቷል።
ፖርቱጋላዊው አማካይ በውድድር ዓመቱ ስምንት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን፥ በተጨማሪም 20 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ በማቀበል የሊጉን ክብረ ወሰን መጋራት ችሏል።
ከዚህ ቀደም ቲዬሪ ሄነሪ (በአርሰናል) እና ኬቨን ደ ብሮይን (በማንችስተር ሲቲ) በነበሩበት ወቅት በተመሳሳይ 20 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል።
ፓርቹጋላዊው አማካይ ቡድኑ ነገ ከብራይተን ጋር በሚያደርገው የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ክብረ ወሰኑን ብቻውን የመያዝ ዕድል አለው።
በተጨማሪም ብሩኖ ፈርናንዴዝ በዘንድሮው የውድድር ዓመት 132 የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የበላይነቱን የያዘ ሲሆን፥ በዚህ ረገድ የሊቨርፑሉ ዶሚኒክ ሶቦስላይ በ89 የጎል ዕድሎች ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ይህንን የፕሪሚየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ክብር ሲያገኝ ከ15 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፥ የመጨረሻው ሽልማት የተመዘገበው እ.አ.አ በ2010/11 የውድድር ዘመን በሰርቢያዊው ተከላካይ ኔማንያ ቪዲች አማካኝነት እንደነበር ይታወሳል።
ፈርናንዴዝ ይህንን ሽልማት ያሸነፈው ከእግር ኳስ ባለሙያዎች፣ ከሊጉ አምበሎችና ከደጋፊዎች በተሰበሰበ ድምፅ ሲሆን፤ ሽልማቱን ለማግኘት ከቀረቡት መካከል ዘንድሮ የሊጉን ዋንጫ ያነሱት የአርሰናል ተጫዋቾች ዴክላን ራይስ፣ ጋብርኤል ማጋሌሽ፣ ዴቪድ ራያ እንዲሁም የማንቸስተር ሲቲውን አርሊንግ ሃላንድ እና አንቶዋን ሴሜኒዮ፣ የኖቲንግሃም ፎረስቱን ሞርጋን ጊብስ-ዋይት እና የሬንትፎርዱን ኢጎር ቲያጎ በብልጫ ማሸነፍ ችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተጫዋቹ ከቀናት በፊት በፈረንሳይና በእንግሊዝ የእግር ኳስ ጸሐፊዎች ማኅበር (FWA) የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ መመረጡ የሚታወስ ሲሆን፥ የክለቡም የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን አግኝቷል።
በተያያዘም የማንቸስተር ሲቲው የ21 ዓመት አማካይ ኒኮ ኦራይሊ የሊጉ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች በመባል ተመርጧል።