ቀጥታ፡

በወሰድነው የምርጫ ካርድ መንግስት ሆኖ ይመራናል፣ ያስተዳድረናል ብለን የምናምነውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል

ባህር ዳር፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ በወሰድነው የምርጫ ካርድ መንግስት ሆኖ ይመራናል፣ ያስተዳድረናል ብለን የምናምነውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።




አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል ገብረስላሴ ሳህሌ እንደገለጹት፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሀገርን የሚመራ መንግስት ለመመስረት የህዝቡ ድምጽ የማይተካ ሚና አለው።

ስለ ምርጫው ሂደትና አስፈላጊነት በቂ ግንዛቤ እየጨበጥኩ በመሆኑ በወሰድኩት የምርጫ ካርድ መንግስት ሆኖ ይመራኛል፣ ያስተዳድረኛል ብዬ ያመንኩበትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።




ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት አበጀ በበኩላቸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይወክለኛል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ምርጫ ማለት የሀገርን እጣ ፈንታ በራስ ድምጽ መወሰን መሆኑን ጠቁመው፤ ፓርቲዎች በሚዲያ በሚያደርጉት ቅስቀሳ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ ይችላል የሚሉትን እየለዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።




7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ የገለጸው ደግሞ ወጣት ደጀኔ አለምነው ነው።

በወሰድኩት የምርጫ ካርድ ለወጣቱ ልዩ ትኩረት የሚሰጠውን፣ ለሀገር ልማትና ዕድገት ይበጃል ያልኩትን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም