ቀጥታ፡

የወንጀል ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ የወንጀል ምርመራ፣ክስና ማስረጃ ሥርዓቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 25/2018 (ኢዜአ)፦የወንጀል ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ የወንጀል ምርመራ፣ ክስና ማስረጃ ሥርዓቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ማዕቀፍ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መረጃ ከ60 ዓመታት በላይ ያገለገለውን የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ የሚተካው የወንጀል ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1410/2018 መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን አመልክቷል።

ባለፉት የሪፎርም ዓመታት ሕገ መንግሥታዊነትን ለማረጋገጥ፣ የመብቶችን ጥበቃ ለማስፋትና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚያስችሉ ሰፋፊ የሕግና ተቋማዊ ማሻሻያዎች የተደረጉ ሲሆን፣ በዚህ ሒደት ከተለዩት ቁልፍ ሕጎች መካከል አንዱ የወንጀል ሥነ ሥርዓት የሕግ መድብል እንደሆነ ገልጿል።

የ1954 የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ ለበርካታ አሥርት ዓመታት በሥራ ላይ የቆየ በመሆኑ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት እና ከወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በዘርፉ ካሉ አዳዲስ አሠራሮችና የቴክኖሎጂ እድገቶች አኳያ ከዘመኑ ጋር በተጣጣመ መልኩ መከለሱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ባለፉት ዓመታት የአዲስ ሕግ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አውስቷል።

ብዙ ምክክር ተደርጎበት የጸደቀው የሕግ መድብል አዳዲስ አሠራሮችን እንደሚያስተዋውቅ የገለጸው ጽህፈት ቤቱ የወንጀል ምርመራ፣ ክስና ማስረጃ ሥርዓቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም