በክልሉ ግብርናን ለማዘመን በተሰሩ ስራዎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ግብርናን ለማዘመን በተሰሩ ስራዎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ሕዳር 30/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ግብርናን ለማዘመን በተሰሩ ስራዎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ ገለጹ።
አቶ አወሉ አብዲ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረሊባኖስ ወረዳ በኩታ ገጠም በመኸር እርሻ የለማን ስንዴ መሰበስብ አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ ዘመናዊ የግብርና የእርሻ ማሽነሪዎች በመጠቀም በተሰሩ ስራዎች ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ላይ ትልቅ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከተረጂነት በመላቀቅ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ እመርታ እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ስንዴን ማምርት ባህል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፤ ይህም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የእርሻ ሥራ ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ግብዓትን ጨምሮ የሚስተዋሉ ሌሎች ማነቆዎችን በመፍታት በግብርናው ዘርፍ እመርታን ለማምጣት ያስቻሉ ስራዎች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ስንዴ ልማት ምርት በየጊዜው እየተሻሻለ እንደሚገኝ ገልፀው፤ አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴን በኩታ ገጠም እና በመስኖ በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የገጠር ሽግግርን በማሳለጥ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።