በዞኖቹ እየተተገበረ የሚገኘው የሻይ ልማት ኢኒሼቲቭ ለገጠሩ ማሕበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ተስፋ የሚጣልበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ እየተተገበረ የሚገኘው የሻይ ልማት ኢኒሼቲቭ ለገጠሩ ማሕበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ተስፋ የሚጣልበት ነው
መቱ ፤ሕዳር 30/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ ቡኖ በደሌና ኢሉአባቦር ዞኖች እየተተገበረ የሚገኘው የሻይ ልማት ኢኒሼቲቭ ለገጠሩ ማሕበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ ተናገሩ።
በዞኖቹ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተተከሉት የሻይ ችግኞች በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን በማንሳት በመጪው ክረምት የሚተከል የሻይ ችግኝ ዝግጅት ከወዲሁ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ ናቸው።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ መንግስት የስራ ሀላፊዎች በኢሉባቦር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተለያዩ የልማት ስራዎች የመስክ ምልከታ እያደረጉ ነው።
አቶ ነመራ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በምዕራብ ኦሮሚያ ሶስት ዞኖች እየተተገበረ የሚገኘው የሻይ ልማት ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በተለይም በጅማ፣ ቡኖ በደሌ እና ኢሉ አባቦር ዞኖች በኢኒሼቲቭ መልክ እየተገበረ የሚገኘው የሻይ ልማት ለገጠሩ ማሕበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ተስፋ የሚጣልበት ነው ብለዋል።
በኢሉአባቦር ዞን በሀሉ ወረዳ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኩታ ገጠም የተተከለ የሻይ ልማት ለሌሎች አካባቢዎችም ምሳሌ የሚሆን መሆኑንም ገልጸዋል።
በቀጣይም የሻይ ልማት ስራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተጀመሩ ስራዎችን የማስፋት ስራ ይከናወናል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው በጅማ፣ ቡኖ በደሌና ኢሉባቦር ዞኖች ባለፈው ክረምት 1 ሺህ 500 ሔክታር መሬት ላይ የተተከለው ሻይ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ልማቱ ያለበት ሁኔታ በሻይ ልማት ኢኒሼቲቩ ላይ የነበረውን ጥርጣሬ የቀረፈ እና አርሶ አደሩም በጥሩ ተነሳሽነት ወደ ስራው እንዲገባ የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል።
የተተከለው ሻይ ለምርት እንዲደርስ ከመንከባከብ ጎን ለጎን የሻይ ምርት የማቀነባበሪያ ፋብሪካ የመገንባት ስራውም ቀጣይ አቅጣጫ መሆኑንም አክለዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የሻይ ልማቱን ለማስፋፋትም በክልሉ በሚቀጥሉት ጊዜያት የሚተከሉ ችግኞችን የማዘጋጀት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተጀመረው የሻይ ልማት ስራ የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።
በዚህ ወቅት ለደረሰው የሻይ ምርት የገበያ ትስስር ከመፍጠር ጎን ለጎን ቀጣይ የሚተከል ችግኝ ዝግጅት መጀመሩንም አስረድተዋል።
በሀሉ ወረዳ ተደራጅተው በሻይ ልማት ስራ የተሰማሩት ወይዘሮ አበበች ደኑና አቶ ዮናስ አረጋ፣ የሻይ ምርታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ተናግረው ቀጣይ ስራውን ለማስፋፋት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።