በጋምቤላ ክልል ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ተመለከተ
ጋምቤላ ፤ህዳር 30/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ለዜጎች ህይወት መለወጥና ለሀገር እድገት ማነቆ የሆነውን ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ተመለከተ።
''ትውልድን በስነ-ምግባር፤ ተቋምን በአሰራር እንገንባ'' በሚል መሪ ሀሳብ 22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በጋምቤላ ክልል ደረጃ ዛሬ በፓናል ውይይት ተከበረ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ዶል ኡኩሪ በመድረኩ ላይ እንዳሉት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የልማትና የዕድገት ፀር የሆነውን ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
ለዜጎች ህይወት መለወጥና ለሀገር እድገት ማነቆ የሆነውን ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮችን በጋራ በመታገል የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል።
በክልሉ ህዝብንና ሀገርን በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግል ዜጋን ለማፍራት እየተከናወነ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም እንዲሁ።
ለሌብነትና ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ አሰራሮችን በማስተካከል እና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤት እያስገኙ እንደሚገኝም ተወካዩ ገልፀዋል።
በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዜጎችን በስነ-ምግባር ማነጽና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ደግሞ ግልጽ በሆነ አሰራር የመገንባቱ ተግባር እንደሚጠናከር ተናግረዋል።
የክልሉ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ቱት ንዑት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሙስናና ብልሹ አሰራሮች የክልሉን ልማትና የህዝቦችን ተጠቃሚነት የሚጎዳ ተግባር ነው።
በመሆኑም ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመታገል መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
የዛሬው የውይይት መድረክም ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በጋራ ለመከላከል ቃላችንን የምናድስበት ጭምር መሆኑንም ገልፀዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።