ቀጥታ፡

በጉራጌ ዞን እየተመዘገበ ያለውን የልማት ስኬት በማስቀጠል የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትጋት እንሰራለን

ወልቂጤ፤ህዳር 30/2018 (ኢዜአ)፦በጉራጌ ዞን በመደመር መንግስት እይታ እየተመዘገበ ያለውን የልማት ስኬት በማስቀጠል የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትጋትና በቅንጅት እንደሚሰሩ የዞኑ አመራሮች ገለጹ።

የመደመር መንግሥት እይታ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን በማረጋገጥና ሁለንተናዊ ለውጥ በማምጣት ህዝብን የልማቱ ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡

ለዚህም በገጠርና በከተማ ያሉ ፀጋዎችን ለይቶ በአዲስ እይታ በማልማት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ትኩረት ስለተሰጠው ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአመራሮች ስልጠና ማጠቃለያ ላይ የመደመር መንግስትን እሳቤ ባስረዱበት ወቅት ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት አዲስ እይታ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በተለይም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብርና ልማት ማከናወን፣ ፆም የሚያድር መሬትን ወደ ምርት መቀየር እንዲሁም የግብርና እና ገጠር ሽግግር እምርታን ማምጣት እንደሚገባም በአፅንኦት ተናግረዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጉራጌ ዞን አመራሮችም በዞኑ ያለውን ዕምቅ ፀጋ በመደመር መንግስት እይታ ወደውጤት በመቀየር ህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትጋትና በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

ለአመራር የተሰጠው ስልጠናም በየአካባቢው የተጀመሩ የልማት ውጥኖችን በትጋትና በላቀ ተነሳሽነት ለመፈጸም አቅም እንደፈጠረላቸው ነው የተናገሩት።

በብልጽግና ፓርቲ የጉራጌ ዞን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል እንደተናገሩት፤ ስልጠናው የልማት አቅምን ለይቶ ወደ ውጤት ለመቀየር የተጀመረውን ጥረት ለማሳደግ የሚያግዝ ነው።

በተለይ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ፣ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም የከተማ ነዋሪዎችን አኗኗር ለማሻሻል የሚያስችል እውቀትና ግንዛቤ በስልጠናው እንዳገኙ ገልጸው፣ በቀጣይም ለህዝብ ተጠቃሚነት ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የሀሳብና የተግባር አንድነትን ፈጥሮ ውጤታማ ልማት በማከናወን በኩል ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ ጉድለቶችን ለማረም በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬታማ የልማት ስራዎችን ለማሳደግም በቅንጅትና በትጋት ለመስራት መዘጋጀታቸውንም አረጋግጠዋል።

በዞኑ በግብርና ዘርፍ ያለን እምቅ አቅም ወደውጤት ለመቀየርና የነዋሪውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ናቸው።

ለዚህም ሳይታረሱ ጾም ያድሩ የነበሩ ማሳዎችና በባህር ዛፍ የለማን ማሳ አንስቶ በተለያዩ ሰብሎች፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና የቅመማ ቅመም ምርቶች ለመሸፈን በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የግብርና ልማት ሥራው ውጤታማነትን ለማረጋገጥ ምርጥ ዘርና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽነት ማጠናከር፣ እንዲሁም ለኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ ትኩረት እንደሚሰጥም አቶ አበራ ተናግረዋል።

ስልጠናው የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ግብአት ያገኙበት እንደሆነ የገለጹት የዞኑ የፋይናንስ መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ሳሊም ከድር በበኩላቸው፣ የዞኑን ልማት በማፋጠን የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም