ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል የሰላምና ፀጥታ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር

ጅግጅጋ ፤ህዳር 30/2018 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የሰላምና ፀጥታ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  ሮዛ ኡመር ተናገሩ።

የምስራቅ እዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ የሐረሪ ክልል የፀጥታ አካላት ዛሬ ተመርቀዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር በምረቃው ላይ ተገኝተው እንዳሉት በክልሉ ሰላምና ፀጥታን የማጠናከር ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።

ለዚህም የፀጥታ ሃይሉ ህዝቡና የሰላም አደረጃጀቶች የሚያከናውኑት የተቀናጀ ስራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ልማትና እድገትን ይበልጥ ለማጎልበትና ሰላምን ለማጽናት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ወይዘሮ ሮዛ አመልክተዋል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ የሀገርን ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት የማስጠበቅ ተልዕኮውን በትጋት እየተወጣ ነው ያሉት ደግሞ የእዙ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄነራል ፍቃዱ ፀጋዬ ናቸው።


 

በተለይም እዙ በቀጠናው ፀጥታና ልማትን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች የሚያከናውነው ስራ ውጤት እያመጣ ይገኛል ብለዋል።

እዙ በቀጠናው እያከናወነ የሚገኘው ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ ለክልሉ ፀጥታ ሃይል ስልጠና በመስጠት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ደግሞ የሐረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ አቶ ተውፊቅ መሀመድ ናቸው።


 

ስልጠናው የክልሉ የፀጥታ አካላት የተሻለ ብቃት እንዲላበሱና እና ወታደራዊ ዝግጁነት እንዲያጎለብቱ የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል። 

በመርሃ- ግብሩ ላይ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ የሐረሪና የሶማሌ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም