በዞኑ ለቱሪዝም ልማት የሚውሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመለየት የማልማት ሥራ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ለቱሪዝም ልማት የሚውሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመለየት የማልማት ሥራ ተጀምሯል
አዳማ ፤ህዳር 30/2018(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ለቱሪዝም ልማት የሚውሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመለየት የማልማት ሥራ መጀመሩን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
የመደመር መንግስት በየአካባቢው ያሉ እምቅ የቱሪዝም አቅሞችን በማልማት ወደ ውጤት እየቀየረ የቱሪዝም ዘርፉንም እያነቃቃ መምጣቱ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በመደመር መንግሥት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል ርዕስ ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በሰጡበት ወቅት "ቱሪዝምን ከቅርስነት ወደ ቁርስነት እንቀይረው፤ ቅርስ ስላለ ብቻ ቱሪስት መጥቶ አያይም፤ ለሚያወጣው ወጪ የሚመጥን አገልግሎት ይፈልጋል፤ የበለጠ ማልማት ያስፈልጋል" ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ በዚሁ መድረክ ላይ አንድ የቱሪስት መዳረሻ በዞን ደረጃ መኖር እንዳለበት አቅጣጫ ያስቀመጡ ሲሆን ሁሉም በየአካባቢው ያለውን እምቅ የቱሪዝም አቅም ለይቶ ማልማት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አባቡ ዋቆ፣ በዞኑ ለቱሪዝም መዳረሻነት የሚውሉ መስህቦችን ለይቶ የማልማት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።
ዞኑ በሰቃ፣ ቆቃና ባቱን ጨምሮ የበርካታ ሐይቆች መገኛ መሆኑን ተናግረው በሐይቆቹ ዙሪያ እና አካባቢው የልማት ስራዎች መከናወን ጀምረዋል ነው ያሉት።
በተለይ በቆቃ ሐይቅ ላይ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን በዚህም ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩን አስረድተዋል።
ሀይቁን ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ከማድረግ አንጻር ዋና ዋና ሥራዎች ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው በሌሎችም ሀይቆች ላይም ስራው ይቀጥላል ብለዋል።
በሌላ በኩል ከገጠር ኮሪደር ልማት አንጻርም በዞኑ እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት የገጠሩን ህዝብ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ አርሶ አደሩ የአኗኗር ዘይቤውን መቀየር እንዲችል የባዮጋዝ፣ የፀሐይ ሃይል፣ መብራት እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ማድረጉን አስረድተዋል።
ከሁሉም በላይ የአርሶ አደሩን የመኖሪያ አካባቢ ውብ እና ማራኪ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው ዘንድሮም ስራው በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።
በአጠቃላይ የግብርና ልማት ሥራ በተለይም በስንዴ፣ ፓፓያ፣ አቮካዶና ሙዝን ጨምሮ በኢኒሼቲቭ መልክ የተገበሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን አንስተዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርም በእንስሳት እርባታ፣ በዶሮ እርባታና በከብት ማድለብ እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።
የግብርና ልማት ስራው ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ግብዓት ሊሆን በሚችል መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አመልክተዋል።
“በመደመር መንግሥት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል ርዕስ የተሰጠው ስልጠናም የበለጠ የአካባቢያቸውን የልማት አቅሞች ወደ ውጤት ለመቀየር ያነሳሳቸው መሆኑን አስረድተዋል።