ቀጥታ፡

ማንችስተር ዩናይትድ ዎልቭስን አሸነፈ

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 29/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ ዎልቭስን 4 ለ 1 አሸንፏል።

ማምሻውን በሞለኒው ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ብሩኖ ፈርናንዴዝ በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ምት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ብሪያን ምቡዌሞ እና ሜሰን ማውንት ቀሪዎቹን ጎሎችን ለዩናይትድ ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ጂን-ራይሰነር ቤልጋርድ ለዎልቭስ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በጨዋታው ላይ ማንችስተር ዩናይትድ በዎልቭስ ላይ ከፍተኛ ብልጫ ወስዶ የተጫወተ ሲሆን ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር የሚችልበትን እድል አልተጠቀመበትም።

በውድድር ዓመቱ ሰባተኛ ድሉን ያስመዘገበው ማንችስተር ዩናይትድ በ25 ነጥብ ደረጃውን ከ12ኛ ወደ 6ኛ ከፍ አድርጓል።

በውድድር ዓመቱ 13ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ዎልቭስ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።

በከፍተኛ ውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ዎልቭስ በሊጉ ምንም ጨዋታ አላሸነፈም።

በውጤቱ እጅጉን ደስተኛ ያልሆኑ አብዛኞቹ የዎልቭስ ደጋፊዎች ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት ስታዲየሙን ለቀው ወጥተዋል።

በ16ኛ ሳምንት ዎልቭስ ከሊጉ መሪ አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ ከቦርንማውዝ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም