ቀጥታ፡

በመንግስት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው

‎ባሕርዳር ፤ ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ) ፡- በመደመር መንግስት እይታ  በተለያዩ  ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራት ሀገራዊ ዕድገቱን ከማፋጠን ባለፈ የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸውን በአማራ ክልል  የሰሜን ጎጃም ዞን እና የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይበይናሉ ተብሎ ትኩረት ከሰጣቸው ዋና ዋና የልማት ዘርፎች ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የከተማና መሰረተ ልማት፣ ማዕድንና ቱሪዝም ይጠቀሳሉ።

የሰሜን ጎጃም ዞን የጎንጂቆለላ ወረዳ  ነዋሪዎች ውስጥ አቶ አዳነ አለምኔ፤ የመደመር መንግስት በግብርናው ዘርፍ ሰፋፊና ውጤታማ የልማት ተግባራት እንዲከናወኑ እያስቻለ ይገኛል ብለዋል።


 

‎‎በተለይ በገጠር ኮሪደር ልማት በግብርናው ዘርፍ በሰብል ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳት እርባታ፣ በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ፣  በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትኩረት ተደርጎ በመስራቱ አበረታች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲመጣ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

‎‎ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት ኋላቀር የሆነውን የግብርና አሰራር በመቀየር በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉም አንስተዋል። 

‎‎በከተማ ልማት ዘርፍ ደግሞ ከተሞችን ፅዱና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

‎‎በቀጣይም ሰላምን አፅንቶ ከማዝለቅ ጎን ለጎን እየተመዘገበ ያለውን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አጠናክሮ ለማስቀጠል የተጀመሩ የልማት ተግባራት ከዳር እንዲደርሱ ሁላችንም የድርሻችንን ለማበርከት መረባረብ አለብን ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ  ወይዘሮ ወለላ የኔው እንደገለጹት፤  የመደመር መንግስት መርሆዎች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልፅግና ፋይዳቸው የጎላ ነው።


 

‎በዚሕም በከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተሞች ፅዱ፣ ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆኑ እያስቻለ መሆኑን አንስተዋል። 

‎‎በተለይ በባሕርዳር ከተማ  የተከናወኑ  የኮሪደር ልማት ስራዎች ባሕርዳር  መርጠው የሚጎበኟት የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ እንድትሆን ማስቻሉን ገልጸዋል። 

‎በቀጣይም በተተኳሪ የልማት መስኮች የተጀመረው የልማት ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን ለማበርከት ዝግጁ እንደሆኑም አረጋግጠዋል። 

‎‎‎በመደመር መንግስት እይታ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በከተማ መሰረተ ልማት ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ተግባራትን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም