ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማስፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 28/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በ5 ከተሞች የተጀመረውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ዳመጠው ገመቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግስት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በሙሉ አቅም ተግባራዊ ለማድረግ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በዚህ መሰረት ክልሉ ለሪፎርሙ ተግባራዊነት ያለውን ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም የሚያስፈልጉ ሰነዶችን በማሟላት የዝግጅት ምዕራፍ አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

በተለይም ሪፎርሙ በክልሉ በፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ፣ በጤና ቢሮ፣ በትምህርት ቢሮ፣ በገንዘብ ቢሮና በአጠቃላይ በ5 የመንግስት መስሪያ ቤቶች በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑንም አንስተዋል።

ከነዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አንዱ ሲሆን የክልሉን ህዝብ ከእንግልትና ካልተገባ ወጪ በማዳን ፈጣን፤ ቀልጣፋና ግልጽነት ያለው የተሻለ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር  ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።


 

ሪፎርሙን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የሰው ሀይል ማሰልጠን ፣ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ ቴክኖሎጂዎቹን ማበልጸግና ግንባታዎችን ማስፋትና ለተገልጋዩ የግንዛቤ ፈጠራ መስጠት ከሚተገበሩት ዋና ዋና ተግባራት መካከል መሆናቸውን አቶ ዳምጠው ገልጸዋል።

በዚህ መሰረት በ2018 በጀት አመት በአንደኛ ዙር በሸገር፤ በቢሾፍቱ፤ በአዳማ፤ በሻሸመኔና ጅማ ከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መጀመሩን አስታውቀዋል።

አገልግሎቱ ከተጀመረ ወዲህ ባለፉት 3 ወራት 180 ሺህ ዜጎች አገልግሎቱን በማግኘት የእርካታ መጠናቸው ከ95 በመቶ በላይ መሆኑን በተደረገ የዳሰሳ ጥናት መለየቱን አንስተዋል። 


 

በክልሉ በበጀት አመቱ አገልግሎቱን አጠናክሮ በማስቀጠል በቀጣይ ከሸገር ከተማ ባሻገር በ13 ትልልቅ ከተሞች ስራው ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

በዚህም በሻኪሶ፣ ሞያሌ፣ ሸኖ፣ ነጆና ዶዶላ ከተሞች እንዲሁም በሁለቱ የአርሲ ዞኖች፤ በጅማ፣ በምስራቅ ሀረርጌና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች  አገልግሎቱ ተደራሽ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

በዘንደሮ አመት በኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ በከንቲባ ደረጃ በሚተዳደሩት በ52 ከተሞች በተሟላ መልኩ አገልግሎቱን ለማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተው በቀጣይ እስከ ቀበሌዎች ድረስ ስራው የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም