በመዲናዋ የግብር ከፋዮችን ቅሬታ አጣርቶ ምላሽ የሚሰጥ አሰራር ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የግብር ከፋዮችን ቅሬታ አጣርቶ ምላሽ የሚሰጥ አሰራር ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ ፤ ሕዳር 22/2018 ( ኢዜአ) ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግብር ከፋዮችን ቅሬታ ሃላፊዎች በተገኙበት አጣርቶ ምላሽ መስጠት የሚያስችል አሰራር ከመጪው ሐሙስ ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
በአዲስ አበባ የግብር አሰባሰብና የገቢዎች አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚኖርን ቅሬታ መፍታት የሚያስችል አዲስ አሰራር በከንቲባ ጽ/ቤት ሥር ተዋቅሯል።
አሰራሩ በአስተዳደሩ የገቢዎች ቢሮ ስር በተዘረጋው የቅሬታ አፈታት ሥርዓት ያልረኩ ግብር ከፋዮች ቅሬታዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ነው፡፡
በዚህ መሰረትም ከገቢ አሰባሰብ፣ ከሠራተኞች ሥነ ምግባርና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚነሱ ቅሬታዎች ዘወትር ሐሙስ ሃላፊዎች በተገኙበት የሚደመጡና ተጣርተው ምላሽ የሚሰጥባቸው ይሆናል፡፡
የተዘረጋው አሰራር ለከንቲባ ጽ/ቤት በሚስጢር ጥቆማ ከሚሰጥበት ነጻ የጥሪ ማዕከል 9977 እና የሚስጢር ሳጥን በተጨማሪ ቅሬታዎችን በአካል ለበላይ አመራር ማቅረብ ያስችላል፡፡
አሰራሩ ከፊታችን ሐሙስ ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባ የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለኢዜአ የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡
ስለሆነም ከመጪው ሐሙስ ሕዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ከገቢዎች ጋር ብቻ የተያያዙ ቅሬታዎችን አመራሩ ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ ተጠቁሟል፡፡