የገበያ ማዕከላቱ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ለገበያ መረጋጋት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገበያ ማዕከላቱ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ለገበያ መረጋጋት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የተገነቡ ትላልቅ የገበያ ማዕከላት አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የገበያ መረጋጋትና ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በመፍጠር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ ከተማ የምርት ፍላጎትና አቅርቦትን በማመጣጠን የፍጆታ ምርቶችን በአንድ ቦታ ለመሸመት አማራጭ የግብይት ማዕከላት አለመኖር ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል።
የከተማ አስተዳደሩ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የገበያውን ሁኔታ ለማረጋጋት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን
ከእነዚህ ውስጥ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ ግዙፍ የገበያ ማዕከላት ግንባታ አንዱ ነው።
በገበያ ማዕከላቱ የግብይት ሥርዓቱ ላይ የነበሩ የተንዛዙ አሰራሮችን ከማስቀረት ባለፈ ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገውን ምርት እንዲያገኝ ዕድል ፈጥረዋል።
በከተማዋ መግቢያ በሮች የተገነቡ የገበያ ማዕከላት የምርት አቅርቦትና ፍላጎትን በማጣጣም ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መፍጠራቸውን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ሸማቾች፣ ነጋዴዎችና አምራቾች ተናግረዋል።
ሸማች ሙሉነሽ ደምሴ እና ዮሴፍ በቀለ በአቅራቢያቸው የተከፈቱ የገበያ ማዕከላት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዳስቻሏቸው ተናግረዋል።
በተለይም የፍጆታ ዕቃዎችን በአንድ ቦታ ላይ ማግኘት መቻላቸው ጊዜና ጉልበት እንደቆጠበላቸው በማንሳት።
በገበያ ማዕከላቱ ምርቶችን የሚያቀርቡ ነጋዴዎች በበኩላቸው ቀደም ሲል የነበረው የግብይት ሰንሰለት የተንዛዛና ለህገወጥነት የተጋለጠ መሆኑን አስታውሰዋል።
በገበያ ማዕከላቱ ከአምራቹ በቀጥታ የሚመጡ ምርቶችን ሸማቹን ማህበረሰብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማስቻሉን የተናገሩት ደግሞ ነጋዴ አበራሽ ወልደሩፋኤል እና ሀጂ ሁሴን የሱፍ ናቸው።
ከአምራቾች መካከል ጉርሜሳ ጀልቀባ በገበያ ማዕከላቱ የግብይት እሴት ሰንሰለቱ እንዲያጥር በመደረጉ የተረጋጋ የምርቶች ዋጋ እንዲኖር አስችሏል ነው ያሉት።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው በከተማዋ የነበሩ አላስፈላጊ የግብይት ሰብሰለቶችን በማስወገድ በከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ አምስት ትላልቅ የገበያ ማዕከላት መገንባታቸውን አንስተዋል።
ማዕከላቱ አላስፈላጊ የንግድ ሰንሰለትን በማሳጠር አምራቹን ነጋዴውንና ሸማቹን በቀጥታ እንዲገናኙ አድርገዋል ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈ በአራት የግብይት ቦታዎች የተጀመረው የቅዳሜና እሁድ ገበያ አሁን ላይ ወደ 219 ከፍ ማለቱ ለገበያ መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ መግቢያ በሮች የተገነቡት 5ቱ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ላፍቶ ሁለገብ የገበያ ማዕከል ቁጥር 1፣ ላፍቶ ሁለገብ ገበያ ማዕከል ቁጥር 2 (ዘመናዊ ሀይፐር ማርኬት እና ሁሉንም የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርች ወዘተ በአንድ ማዕከል ያየዘ)፣ ለሚ ኩራ የገብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል፣ ኮልፌ የገብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል፣ አቃቂ ቃሊቲ የገብርና ምርቶች የገበያ ማዕከላት ናቸው።
የገበያ ማዕከላቱ ዘመናዊ የግብይት ስርዓት እንዲኖር በማድረግ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት እንዲሰፍን እያስቻሉም ይገኛሉ።