ቀጥታ፡

የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል

ሚዛን አማን፤ ሕዳር 22/2018(ኢዜአ)፦ በቤንች ሸኮ እና በወላይታ ዞኖች ያሉትን የልማት አቅሞች በመጠቀም የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መትጋትና የመንግሥት ተግባራትን በቁርጠኝነት ማከናወን ከአመራሩ እንደሚጠበቅ ተገለጸ።

"በመደመር መንግሥት ዕይታ፤ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ በዞኑ ሚዛን አማን ከተማ አጠቃላይ የአመራር ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል።

በመድረኩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደግፌ ኩድን እንዳሉት፤ የብልጽግና ጉዞ በኅብረተሰቡ ሕይወት ውስጥ ውጤት እያመጣ እንዲቀጥል ብቃት ያለው አመራር መፍጠር ያስፈልጋል።

በተለይ የአካባቢ ጸጋን መለየትና የመልማት ዕድልን ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ብለዋል።


 

ለዚህም ፓርቲው የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን እየሰጠ ሲሆን አሁን ላይ የሚሰጠው ሥልጠና ልማትና የተግባር ውጤታማነት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።

ዞኑ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ያለው ምቹ ሁኔታ ትርጉም እንዲኖረው የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማስፋፋትና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ተግባርን በስኬት መምራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይም በዞኑ ያለውን የልማት አቅም በመጠቀም የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መትጋት ከአመራሩ ይጠበቃል ብለዋል።


 

በተመሳሳይም በወላይታ ዞን "በመደመር መንግስት እይታ፤ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ የ3ኛ ዙር የአመራሮች ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል። 

በመድረኩ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ ፤በዞኑ በሁሉም ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ እመርታዊ ለውጦችን ለማስቀጠል የአመራሩን አቅም ማጎልበትና ብቁ አመራር መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል። 


 

በግብርናና በገጠር ትራንስፎርሜሽን፣ በቱሪዝም፣ በከተማ ልማት እና በኢንዱስትሪ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብና ዕድገቱን ለማስቀጠል በአመራሩ መካከል የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ሊኖር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ትርክትን በማስረጽ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በቅርበት ተከታትሎ ለመመለስ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም በአጽንኦት ተናግረዋል። 

በሥልጠናውም ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳና ከከተማ አስተዳደር የተወጣጡ ከአንድ ሺህ 100 በላይ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም