ቀጥታ፡

የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

ደብረ ብርሃን/ ኮምቦልቻ ፤ ሕዳር 22/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል  የፖሊስ ሰራዊትን አቅም በመገንባት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሰላምን ለማፅናት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን  የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በደብረብርሃን እና ኮምቦልቻ  ከተሞች በተቋማዊ ሪፎርም አፈፃፀም፣ በጂኦ ስትራቴጂና የፖሊስ አመራር አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ መድረክ እያካሄደ ነው።

በደብረብርሃን በተካሄደ መድረክ በጠቅላይ መምሪያው የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል አበበ ውቤ ፤  የፖሊስ አባላቱ   ፀጥታን በማስከበር  ልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የበኩላቸውን  እየተወጡ  መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በዚህም በክልሉ  ሕግና ፍትህን ለማረጋገጥ  በቅንጅት በመስራት የሕብረተሰቡን  የልማት ጥያቄዎች  እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል።

በክልሉ በተደረገው የፖሊስ ሪፎርም  በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አመልክተው፤ ይህም የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንና  የተጀመረው ስልጠናም  የፖሊስን  አቅም ይበልጥ የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን  ዋና አስተዳዳሪ አቶ  መካሻ  ዓለማየሁ በበኩላቸው፤  የባዳና የባንዳዎችን እኩይ ሴራ በማምከን  ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።


 

የፖሊስ አባላቱ  ከስልጠናው የሚያገኙትን  እውቀት በመጠቀም የበለጠ እንዲሰሩም አሳስበዋል። 

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፤   መንግስት  የልማት ፣ የሰላምና  የመልካም አስተዳደር ስራዎችን  እያቀላጠፈ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይህንን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል  የፖሊስ አባላት  ሕግን በማስከበር ሰላምን ለማፅናት የሚሰጣቸውን የአቅም ግንባታ ስልጠና ወደ ተግባር በማሸጋገር ሚናቸውን በብቃት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ በተካሄደው መድረክ የተገኙት በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጄኔራል ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀው እንደገለጹት፤ በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

የፖሊስ ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማዘመንና በሪፎርም በማደራጀት የሕግ የበላይነትን  ለማረጋገጥና ሰላምን ለማፅናት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

የፀጥታ አመራርና አባላትን እውቀትና ክህሎት በማሳደግ ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አሳምን ሙላት በበኩላቸው፤  በዞኑ የሰፈነውን ሰላም  በማፅናት የልማት ስራዎች በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።


 

ዛሬ የተጀመረው ስልጠናም እውቀትና ክህሎታችንን በማሳደግ የተሻለ እንድንሰራ እድል ይፈጥርልናል ብለዋል።

በስነ ምግባር የታነፅ ብቁ የፖሊስ አመራርና አባላት በመፍጠር  የዞኑን ሰላም ለማፅናት በየደረጃው ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ፋንቱ ተጋፋው ናቸው።


 

በዚህም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው፤  ይህንን ውጤት አስጠብቆ  ለማስቀጠል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ጌታቸው ሙህዬ ፤ ከሕብረተሰቡ ጋር  በመቀናጀት  የከተማውን ሰላም መጠበቅ በመቻሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

ሕግን በማስከበር የከተማውን ሰላም አፅንቶ ልማትን ለማስቀጠል ስልጠናው እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።


 

በሁለቱ ከተሞች እየተሰጠ ባለው ስልጠና  ከሰሜን ሸዋ ፣ ፣ ከደቡብና ሰሜን  ወሎ ዞኖች ፣ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ከዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፣ ከደብረብርሃን ፣ ከወልዲያ፣ ከደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ  የፀጥታ አመራሮችና አባላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም