ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ ሀገር በመገንባት ሂደት አሰባሳቢ ትርክት ላይ ይበልጥ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ ሀገር በመገንባት ሂደት አሰባሳቢ ትርክት ላይ ይበልጥ መስራት ይገባል
ነቀምቴ፤ ሕዳር 22/2018(ኢዜአ)፦ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ ሀገር እንዲገነባ አሰባሳቢ ትርክት ላይ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ ተመለከተ።
20ኛው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በነቀምቴ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ መሰረት ሀይሉ በፓናል ውይይቱ ላይ እንዳሉት፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ወሳኝ ነው።
ብሔሮችና ብሔረሰቦች በአንድነት የሚኖሩባት ነቀምቴ በነዋሪዎቿ ተሳትፎ በከተማ አስተዳደሩ የመንግስት የልማት እቅዶችም በታቀዱት መሰረት እየተተገበሩ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም የከተማው ነዋሪ አንድነቱን አጠናክሮ የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅና የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል የተናገሩት ከንቲባው በተለይም ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አገር እንዲገነባ አሰባሳቢ ትርክት ላይ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የነቀምቴ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ መሰረት ሀይሉ በበኩላቸው፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር በህዝቦች መካከል ፍቅርና መከባበርን በማጎልበት ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር የጎላ ሚና አለው ብለዋል።
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በነቀምቴ ከተማ መከበሩም የህዝቡን የእርስበርስ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑንም አስረድተዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የነቀምቴ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ መላኩ ጌታሁን በበኩላቸው፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ እሴቶች ላይ በትኩረት በመስራት ለሀገር እድገት መረባረብ ይገባል ብለዋል።
የበለፀገች ሀገርን ለቀጣይ ትውልድ ለማውረስ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ሳይደናቀፉ መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተው የከተማው ነዋሪ ሰላሙን መጠበቅ እና አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት በሆሳዕና ከተማ እንደሚከበር ይታወቃል።