በማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦ በማዕድን ዘርፍ ያለውን እምቅ ሀብት ወደ ብልፅግና ለመቀየር መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር) ገለፁ።
በማዕድን ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከህዳር 4 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው 4ኛው ዓለም አቀፍ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ(MINTEX Ethiopia 2025) በስኬት እንዲጠናነቅ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና እና የመዝጊያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኘ(ኢ/ር) እንዳሉት በማዕድን ዘርፍ ያለውን እምቅ ሀብት ወደ ብልፅግና ለመቀየር መንግስት በዘርፉ ለሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው።
ባለፉት አመታት የማዕድን ዘርፉን ተግዳሮት ለመፍታት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም ነው የተናገሩት።
ለማዕድን ኢንዱስትሪው በተሰጠው ትኩረት ምክንያት በማዕድን ሀብት ማስተዋወቅ እና በፕሮጀክት አስተዳደር ላይ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑንም ገልጸዋል።
ባለፉት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ኤክስፖ ትምህርት የሚሰጡ ጥናቶች መቅረባቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የማዕድን ዘርፉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት የሚያሳልጥ በመሆኑ ያለንን እምቅ ሀብት ወደ ብልፅግና ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ ኢንቨስተሮች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፉ መሰማራት ከሚፈልጉ ኢንቨስተሮች ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላትም ነው የተናገሩት።
በምስጋና እና መዝጊያ መርሃ ግብሩ ለኤክስፖው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷል።
አራተኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (MINTEX Ethiopia 2025) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ መከፈቱ ይታወቃል።