ቀጥታ፡

በሰው ተኮር የልማት መርኃ ግብር የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እየተሰሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦በሰው ተኮር የልማት መርኃ ግብር የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ መሐመድ አሚን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ዛሬ በኮምቦልቻ ሪጆፖሊታን ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ የዲጂታል አገልግሎት ፣ የዘመናዊ የሥራ ቦታ እድሳት እና ሰው ተኮር ተግባራትን ጎብኝተዋል።


 

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ዋና ከንቲባ መሐመድ አሚን በዚሁ ወቅት፤ ስማርት ኮምቦልቻን እውን ለማድረግ በርካታ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስማርት ኮምቦልቻን እውን ለማድረግ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የደህንነት ካሜራ ተከላ፣ የትራፊክ እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ እና የከተማዋን አገልግሎት አሰጣጥ ኢ-ሰርቪስ ማድረግ እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ስራዎች ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ስማርት ኮምቦልቻ እውን ትሆናለች ብለዋል፡፡


 

ከተማዋን የማዘመን እና የነዋሪዎቿን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ሰው ተኮር የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሰው ተኮር ስራዎች ነዋሪዎችን የስራ እድል፣ ተማሪዎችን ደግሞ የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከበጎ አድራጊዎች ጋር በመተባበር በ43 ሚሊዮን ብር አዲስ ቤት በማስገንባት ለአቅመ ደካሞችና ለአገር ባለውለታዎች ማስረከቡን ጠቅሰዋል፡፡


 

በቀጣይም ከተማዋን የማዘመንና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

መኖሪያ ቤት ከተሰጣቸው መካከል አንዷ ወይዘሮ ሰናይት ሞላ፤ የስፌት ስራ በመስራት ከሚያገኙት ገንዘብ  በመቀነስ የግል ቤት ተከራይተው ይኖሩ  እንደነበር በመጠቆም ቤት በማግኘታቸው እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ 


 

በጡረታ የተገለሉት ዋና ሳጅን አበጋዝ አሊ በበኩላቸው፤ የግል ቤት ተከራይተው ይኖር እንደነበር በማስታወስ መንግስት በጨነቀኝ  ሰዓት ደርሶልኛል ሲሉ ደስታቸውን አጋርተዋል፡፡ 


 

ሌላኛዋ የቤት ተጠቃሚ የሻረግ እርቅይሁን በበኩላቸው፤ መንግስት ከአስቸጋሪው የኪራይ ህይወት አውጥቶ የቤት ባለቤት እንዳደረጋቸው በመናገር ለተደረገላቸው ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም