የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሁሉም አካል ርብርብ አስፈላጊ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሁሉም አካል ርብርብ አስፈላጊ ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሁሉም አካል ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአፍሪካ የመንገድ ደህንነት ቀን ዛሬ ህዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ እና የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሁሉም አካላት ርብርብ አስፈላጊ ነው።
በአፍሪካ በየዓመቱ የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው ኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው ብለዋል።
ለአብነትም በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የመንገድ ደህንነት እንዲጠበቅ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ለእግረኞች፣ለብስክሌት እንዲሁም ለተሽከርካሪ ምቹ የሆኑ መንገዶች እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
በአገሪቱ የመንገድ ደህንነትን የሚያስጠብቁ የህግ ማዕቀፎች መውጣታቸውን አስታውሰው ለትራፊክ አደጋ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማት እና ኢነርጂ ኮሚሽነር ሌራቶ መተቦጌ በበኩላቸው እንደገለጹት በአፍሪካ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ።
ኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የጀመረችው ጥረት የሚበረታታ እና ለሌሎች አገራት ምሳሌ መሆን የሚችል ነው ብለዋል ።
በአፍሪካ የመንገድ ደህንነትንና ዘላቂ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ለማረጋገጥ የበለጠ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በአፍሪካ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እንደሚከሰት ጠቁመው ኮሚሽኑ አደጋውን ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንገድ ደህንነት ቀን የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች የሚታወሱ መሆኑን በመጠቆም እ.አ.አ በ2030 በአህጉሪቱ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ሞት በ50 በመቶ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አባሶ በበኩላቸው እንደገለጹት የትራፊክ አደጋ በአገር ሰብዓዊ ሃብትና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።
ችግሩን ለመፍታት የሁሉም ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው ህግ ለማስከበር የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
በአገሪቱ ያለው የተሽከርካሪ ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም የሚደርሰው አደጋ ግን ከፍተኛ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ችግሩን ለመፍታት በቀጣይ ጠንካራ ስራ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በአገሪቱ በየደረጃው የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ህብረት እ.አ.አ 2012 ባሳለፈው ውሳኔ ቀኑ በየዓመቱ የሚከበር ሲሆን እለቱ ከዓለም የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች መታሰቢያ ቀን ጋር እንዲተሳሰር መደረጉ ተገልጿል።