ታካሚዎች በጤና መድኅን አገልግሎት በአነስተኛ ክፍያ ከፍተኛ ሕክምናዎችን ጭምር እያገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታካሚዎች በጤና መድኅን አገልግሎት በአነስተኛ ክፍያ ከፍተኛ ሕክምናዎችን ጭምር እያገኙ ነው
ሀዋሳ፤ ህዳር 7/2018(ኢዜአ)፦በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት በአነስተኛ ክፍያ ከፍተኛ የሕክምና አገልግሎቶችን ጭምር አግኝተናል ሲሉ በሲዳማ ክልል የጤና መድህን አባላት ተናገሩ፡፡
በሲዳማ ክልል ይርጋዓለም ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ማህደር ታምራት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት አባል ከሆኑ ከ10 ዓመት በላይ እንደሆናቸው ይገልጻሉ፡፡
በነዚህ ጊዜያት እርሳቸውና ቤተሰቦቻቸው በዓመት በሚከፍሉት አነስተኛ ክፍያ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስወጡ የሕክምና አገልግሎቶችን ጭምር እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ልጃቸው በይርጋዓለም ሆስፒታል ያለተጨማሪ ወጪ የቀዶ ሕክምናና ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን ማግኘቱን ተናግረዋል።
በጤና መድህን አገልግሎት ከመድኃኒት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች ተፈተው የተሻለ አገልግሎት እያገኘን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በይርጋለም ሆስፒታል የተኝቶ ሕክምና አገልግሎት እያገኘ ያለው የዳሌ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ደጀኔ ደረሰ በሥራ ላይ ባጋጠመው አደጋ ምክንያት በጀርባ አጥንቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግሯል፡፡
የማህበረሰብ ጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆኑ ለአንድ ዓመት በሚጠጋ ጊዜ በሆስፒታሉ ያለ ተጨማሪ ወጪ የተሟላ ሕክምና እያገኘ መሆኑን ገልጿል።
ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ መቀመጥም ሆነ ከወገቤ በታች አካሌን ማንቀሳቀስ አልችልም ነበር ያለው ወጣት ደጀኔ ባገኘው ሕክምና አሁን ላይ ራሱን ችሎ መቀመጥና በድጋፍ መሳሪያ ታግዞ መንቀሳቀስ መጀመሩን ተናግሯል።
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ይስሀቅ መርክነህ በበኩላቸው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አባል በመሆን ለዓመታት ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
የጤና መድህን አገልግሎቱ በእጅ እንዳለ ጥሬ ገንዘብ ነው የሚሉት አቶ ይስሀቅ እርሳቸውን ጨምሮ የስኳርና የደም ግፊት ታካሚ የሆኑት ባለቤታቸውና ልጆቻቸው በአነስተኛ ዓመታዊ ክፍያ ያለስጋት መታከም እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትልና የሕክምና አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙንጣሻ ብርሀኑ በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎትን በማስፋት ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
አገልግሎቱን ለማስፋት በተሰጠው ትኩረት የተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው በ2017 በጀት ዓመት ከ412 ሺህ በላይ አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ሽፋኑን 72 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
ዘንድሮ ነባር አባላትን ጨምሮ ከ670 ሺህ በላይ አባወራና እማ ወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የምዝገባና የአባልነት እድሳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ኃላፊ ገለጻ የጤና መድኅን አገልግሎት ጥራትና ግብዓት አቅርቦት በዘላቂነት ለማሻሻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ከጤና ጣቢያ ጀምሮ አገልግሎቱን የሚሰጡ ሁሉም ተቋማት በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ መሰራቱን አውስተዋል፡፡