የትምህርት ጥራትን አግባብነትና ፍትኃዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን አግባብነትና ፍትኃዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ የትምህርት ጥራትን፣ አግባብነትንና ፍኃዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ቋሚ ኮሚቴው የትምህርት ሚኒስቴርን የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
የትምህርት ሚኒስቴር ስትራቴጂክ ጉዳየች ስራ አስፈጻሚ እሸቱ ገላዬ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት በበጀት አመቱ ሶስት ወራት የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናችውን ተናግረዋል።
በተለይ በትምህርት ትውልድ ንቅናቄ እንዲሁም ፈተናዎችን በኦንላይን ለመስጠት እየተሰራ ያለውን ስራን ለአብነት አንስተዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መንግስት የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ስራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቶችንና የመምህራንን አቅም ማሳደግን ጨምሮ ሌሎች በዘርፉ ስኬት ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተከናወኑት ተግባራትም ውጤት እየታዩ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
እየተቀየረ ያለው የትምህርት አቅጣጫ ውጤታማ ዜጋ የሚፈጠር በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው አክለዋል።
በግምገማው የቋሚ ኮሚቴው አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን በፕሮጀክት ግንባታ እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ራስ ገዝነት ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ወደ ራስ ገዝነት ለማስገባት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከፕሮጀክት አፈጻጸም አኳያም የተመረጡ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል ውጤትን ለማሻሻል በየደረጃው እየተከናኑ የሚገኙ የክትትልና የቁጥጥር ስራዎች በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ምንም ተማሪ ያላሳለፉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አቅም ለማሳደግ በትኩረት መሰራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
በአጠቃላይ የትምህርት ጥራትን አግባብነትና ፍትሃዊነትን የማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡