በመንግሥት በሕዝብ እና በባለሀብቶች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን መደገፍ የምንፈልገውን ብልጽግና ለማምጣት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
በመንግሥት በሕዝብ እና በባለሀብቶች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን መደገፍ የምንፈልገውን ብልጽግና ለማምጣት ያስችላል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2018(ኢዜአ)፦ በመንግሥት፣ በሕዝብ እና በባለሀብቶች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን መደገፍ እና መንከባከብ የሚፈለገውን ብልጽግና ለማምጣት እንደሚያስችል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ያለ ዕውቀት የሚሠራ ሀገር የለም በሚል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ከሐይቅ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ጎን ለጎን በባለሀብቱ በላይነህ ክንዴ የተገነባውን "ገበታ ለትውልድ ሐይቅ ቁጥር 1 አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት" መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የፈረሰው የጭቃ ትምህርት ቤት ይሠራልን ብሎ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለዓመታት የጠየቀውን ጥያቄ አቶ በላይነህ ክንዴ እንደመለሱ ጠቅሰው ለዚህም ላቅ ያለ ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል።
ልማት ውጤቱ መልከ ብዙ ነው። በአንድ አካባቢ የሚደረግን ማንኛውንም ዓይነት ልማት ከደገፍነውና ከተንከባከብነው አካባቢውን በአንድም በሌላም መንገድ ይቀይረዋል ነው ያሉት።
የሐይቅ አካባቢ ሕዝብ የሚሠራውን የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት በመደገፉና ሰላሙን በማስከበሩ የትምህርት ቤት ግንባታውን ማስጨመሩን አመልክተዋል።
ዛሬ ከአብርሆት ቤተ መጻሕፍት የተገኙ 4 ሺህ 250 መጻሕፍት ለትምህርት ቤቱ ቤተ መጻሕፍት ማስረከባቸውን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም የልማቱና የሰላሙ ትሩፋት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በየአካባቢው በመንግሥት፣ በሕዝብ እና በባለሀብቶች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በመንከባከብ፤ በመደገፍ፣ ዕንቅፋቶችን በማንሳት እና እንዲሳኩ ከጎናቸው በመቆም ባለ ብዙ አትራፊዎች መሆን እንችላለን ብለዋል።
እንደ አቶ በላይነህ ክንዴ ያሉ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ማኅበራዊ ችግሮችን የሚፈቱ ባለ ሀብቶች በበዙ ቁጥር ብልጽግናችን ፈጣን ይሆናል ሲሉም ነው የገለጹት።
እንደ ሐይቅ አካባቢ ሕዝብ ልማትና ሰላምን የሚከባከብ ማኅበረሰብ እየበዛ በመጣ ቁጥር ችግሮች ታሪክ ይሆናሉ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።