በአማራ ክልል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ሆነዋል
ደሴ፤ ሕዳር 5/2018(ኢዜአ)፡ - በአማራ ክልል በክረምት የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው "በጎነት ለጤናችን" በሚል መሪ ሃሳብ የ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ ማጠቃለያ፣ የበጋ ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያና የእውቅና አሰጣጥ መድረከ በደሴ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልከሪም መንግሥቱ እንደተናገሩት፤ በመደበኛ ከሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ በክረምቱ በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ይህም ከፍለው መታከም የማይችሉ ከ6ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግና ከ82 ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
በክረምቱ የተገኘውን ተሞክሮ በማስፋት በበጋው ወራትም ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጠል የጤና ባለሙያዎችና ሕብረተሰቡን በማስተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአገልግሎቱ እስከ ከፍተኛ ቀዶ ሕክምና ጭምር መስጠት መቻሉን ጠቁመው፤ ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና ጤና ተቋማት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋ ሞላ በበኩላቸው፤ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጤና ተቋማትና ጤና ባለሙያዎችን በማስተባበር ለበርካታ አቅመ ደካሞች ሕክምና በነጻ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በክረምት የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በበጋው ወራትም ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በደሴ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ የሕክምና ተሃድሶና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተባባሪ ሲስተር ውብእጅግ ወርቅነሕ እንዳሉት፤ በክረምቱ የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት በከተማው ከ16 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
አገልግሎቱን በበጋውም ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የተሰጠን እውቅና የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
በእውቅና አሰጣጡ መድረክ ላይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደረ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።