በዓሉ የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለመላው ዓለም የምናሳይበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉ የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለመላው ዓለም የምናሳይበት ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡-የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለመላው ዓለምና ለኢትዮጵያዊያን የምናሳይበት ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር ገለፁ።
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ''ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኀብረብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይከበራል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፌዴራል የበዓሉ አቢይ ኮሚቴ 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ዝግጅትን ገምግሟል፡፡
በግምገማ መድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፌዴራል የበዓሉ አቢይ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የበዓሉ ሁነቶች የሚከናወንባቸው ስፍራዎች፣ የእንግዶች ማረፊያ ቦታዎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የከተሞች የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ያከናወናቸው የዝግጅት ስራዎች ተገምግሟል።
በግምገማ መድረኩ እንግዶች የሚያርፋባቸው ሆቴሎች ተለይተው ደረጃቸውን አሟልተው መዘጋጀታቸው ተብራርቷል።
እንዲሁም የሆሳዕና ከተማ ሲፖዚየም የሚካሄድበት አዳራሽ፣ በወልቂጤ ከተማ የንግድ ኤግዚብሽን እና ባዛር ስፍራ ግንባታ መጠናቀቁም ተመላክቷል፡፡
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዓሉን በባለቤትነት ይዞ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ጥሩ ዝግጅት ማድረጉ አንስተዋል። ያየናቸው የልማት ስራዎች የበዓሉ ትሩፋቶች መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
በዓሉ የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለመላው አለምና ለኢትዮጵያዊያን የምናሳይበት ነው ያሉት አፈ ጉባኤው በዓሉን በተሳካ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችሉ ቀሪ ስራዎች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የህዝቡን አንድነት በማጠናከር የመቻቻል እና የመከባበር እሴቶች እንዲጎለብቱ በዓሉ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረክታል ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ናቸው።
እንግዶችን በአግባቡ ተቀብሎ በዓሉ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መሰረት አድርጎ እንዲከበር የክልሉ መንግሥትና ህዝብ በሁለንተናዊ መልኩ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል። ቀሪ የዝግጅት እና የልማት ስራዎችን በ15 ቀን ውስጥ ማጠናቀቅ እንደሚቻል አረጋግጠዋል።
በዓሉ ከተስፋ ብርሃን ተሸጋግረን ወደ ሚጨበጥ ተስፋ ላይ መድረሳችንን የምናሳይበት ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በዓሉ የአብሮነታችንና የህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ማሳያ በመሆኑ በድምቀት ለማክበር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ተብሏል።
በበዓሉ ሲምፖዚየሞች፣ ባዛሮች፣ የውይይት መድረኮች እና የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ተጠቁሟል ።