በመደመር መንግሥት ዕሳቤ ሁሉም ተቋማት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን የመተግበር ግዴታ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በመደመር መንግሥት ዕሳቤ ሁሉም ተቋማት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን የመተግበር ግዴታ አለባቸው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 5/2018 (ኢዜአ)፡-በመደመር መንግሥት ዕሳቤ ሁሉም ተቋማት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን የመተግበር ግዴታ እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ አስታወቁ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የተሞክሮ ልውውጥ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ሪፎርሙ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደርን በሚፈለገው ልህቀት ማስቀጠል የሚያስችል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የመደመር መንግሥት ዕይታ ለዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው ስልጠና ወቅት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ እንዳለበት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ዕሳቤ ተቋማት ዘመናትን የሚሻገሩ ዘላቂና እኛን መምሰል አለባቸው በሚል በግልጽ መቀመጡን ገልጸዋል።
በመሆኑም ሪፎርሙ በሀገራዊ ዕሳቤ የተቃኘ፣ ከሀገራዊ እሴት የተቀዳ መሆኑን አመልክተው፤ በሁሉም ተቋማት ገቢራዊ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ሪፎርሙ በሦስት ምዕራፎች ሲከፈል የተሻለ አፈፃፀም፣ መካከለኛና ወደኋላ የቀሩትን በመለየት መሆኑን አንስተው፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተሻለ አፈፃፀም አስመዝግቦ በግልጽ መመረጡን ተናግረዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ በሶስት ምዕራፍ የተለየበት ሌላው መንገድ ተቋማት ከመጀመሪያዎቹ ልምድ እየወሰዱ በተሻለ መፈፀም እንዲችሉ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ሂደቱ በሰባቱ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ምሰሶዎች አኳያ መታየት እንዳለበት ጠቁመው፤ ሁሉም ተቋማት ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ሪፎርሙ በዘመናት መካከል የፀና ተቋም የመገንባት ዓላማ መያዙን ገልጸው፤ ሪፎርሙን በሂደት ማሻሻልና ማሳለጥ ይገባል ብለዋል።
በዚህም የመጀመሪያ ምዕራፍ ተቋማት ወደ ትግበራ፣ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ ያሉት ደግሞ ወደ ዝግጅት በፍጥነት መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለሪፎርሙ ስኬት ምቹ የሥራ ቦታ መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ የሰራተኛው ምዘና ከሥራው ዓይነትና ባህርይ ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ተቋማት የሰራተኞችን አቅም ለመለየት፣ ለመመዘንና ለማብቃት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚከተለው አሰራር ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምዘና ወቅት ስራውን በአግባቡ ሳይረዳ የሚሰራ ባለሙያ እንዳለ አረጋግጠናል ያሉት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሯ፤ ምዘናው የሰራተኛውን ጉድለቶች ለይቶ መሙላት ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።