ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ሀይል በመጠቀም የህዝቡን ኑሮ የማሻሻል ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ሀይል በመጠቀም የህዝቡን ኑሮ የማሻሻል ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)
ቦንጋ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ህብትና የሰው ሀይል በአግባቡ በመጠቀም የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የሚከናወኑት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በበጀት ዓመቱ በንቅናቄ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ከክልሉ አመራር አባላት ጋር መክረዋል።
በመድረኩ እንዳሉት፥ ያለንን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ሀይል በተገቢው በመጠቀም ለህዝቡ የመልማት እድል መፍጠር በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በገጠር ኮሪደር የተጀመሩ ስራዎችን ጥራት ማስጠበቅና ተደራሽነትን ማስፋት፣ ዘመናዊ የገጠር መንደሮችን መፍጠር፣ የከተማ ኮሪደር ልማትን አጠናከሮ ማስቀጠል ደግሞ ከትኩረት አቅጣጫዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በከተሞች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ ማድረግ፣የከተማ ግብርናና የግብይት ማዕከላትን መገንባትም ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን አንስተው፤ በግብርናው ዘርፍም ምርታማነትን ለማሳደግ የግብዓት አጠቃቀምን በማሻሻል ዘመናዊ አሰራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ፣በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎችም ተሞክረው ውጤት ያመጡ ተግባራትን በአርዓያነት በመውሰድ ለመስራት ታቅዷል ብለዋል።
አክለውም፥ አመራሩ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎችን ለመፈፀም በቅድሚያ የራሱን የስራ ባህል መቀየርና ተግባራትን በቁርጠኝነት መፈፀም ላይ ማተኮር እንዳለበትም አሳስበዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፥ የግብርናና ገጠር ልማት ሽግግርን ውጤታማ ለማድረግ ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ለዚህም የሚለማውን የማሳ ሽፋን ከማሳደግ ባሻገር ግብዓት አጠቃቀምን ማሳደግና ዘመናዊ አሰራርን መከተል እንደሚገባ ገልጸው፥ ሊታረስ ከሚችለው ማሳ ውስጥ 25 በመቶው በኩታ ገጠም እንደሚታረስ ተናግረዋል።
በተለይም የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ያለውን ክፍተት ፈጥኖ ማረም ላይ አመራሩ በልዩ ትኩረትና ቁርጠኝነት ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን እንዳሉት፥ ሁሉም አመራር ለብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ ለማሳካት እቅዶችን በላቀ ደረጃ ለመፈፀም በቁጭት ወደ ተግባር መግባት አለበት ብለዋል።
ክልሉ ያለውን ሰፊ የመልማት ፀጋዎች በተገቢው ለይቶና አውቆ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት የአመራሩ ቀዳሚ ተልዕኮ መሆኑን ጠቁመዋል።