ቀጥታ፡

በዓሉን ስናከበር የሕገ መንግስቱንና የፌዴራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ላይ የሕብረተሰቡን ግንዛቤን ይበልጥ በማሳደግ ሊሆን ይገባል

ባሕርዳር፤ ሕዳር 3/2018(ኢዜአ)፡- የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ስናከብር  የሕገ መንግስቱንና ፌዴራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ላይ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ  ይበልጥ  በማሳደግ ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ። 

20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በሕገ -መንግስትና በፌዴራሊዝም ጽንሰ-ሃሳብ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የህግ ጉዳዮች ዋና አማካሪ አቶ ይርሳው ታምሬ በመድረኩ ላይ እንዳመለከቱት፤ ሕገ-መንግስቱ በምርጫ ተወዳድሮ በማሸነፍ የመንግስት ስልጣን የሚያዝበት፤ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች የሚረጋገጡበት ሰነድ ነው።

በዓለም ላይ ያሉ የበርካታ ሀገራት ስኬት ምንጩ በህገ-መንግስት በመመራታቸውና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በማስፈናቸው መሆኑን አንስተዋል።

እኛም የምንከተለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እያመጣ ያለውን ለውጥ በመገንዘብና ይበልጥ ስር እንዲሰድ አበክረን መስራት አለብን ብለዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን ስናከብርም የሕገ-መንግስቱንና ፌዴራላዊ ጽንሰ ሃሳብ ላይ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ይበልጥ በመሳደግ ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል የአደጋ ስጋት አመራር ምክትል ኮሚሽነር ሰርክአዲስ አታሌ በበኩላቸው፤ ብዝሃነትን መሰረት ያደረገ የሕብረ ብሔራዊ  ፌደራሊዝም ሥርዓት በፍትሃዊነትና በእኩልነት ለማስተዳደር ተመራጭ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በሀገራችን እየተተገበረ ለሚገኘው የፌደራሊዝም ሥርዓት መሰረት የሆነውን ሕገ መንግስት በአግባቡ በመገንዘብ  ለተግባራዊነቱ ይበልጥ መትጋት እንደሚገባ አስረድተዋል።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩም በሕገ-መንግስትና በፌዴራሊዝም ሥርዓት ጽንሰ ሀሳብ ላይ ሰፊ ውይይት በማካሄድ የጋራ ግንዛቤ ለመጨበጥ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

 ስለ ሕገ መንግስቱና ፌዴራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ በዓላትን እየጠበቁ ብቻ ሳይሆን የግንዛቤ ፈጠራና የማስረጽ ስራው የዘወትር ተግባር መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በትግሉ ተስፋሁን ናቸው።

“ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ  የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም