የአብሮነት እሴቶችን በመጠቀም የሰላም ግንባታ ሚናችንን እናጠናክራለን-የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአብሮነት እሴቶችን በመጠቀም የሰላም ግንባታ ሚናችንን እናጠናክራለን-የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች
ደብረ ብርሃን፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦ የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶችን በመጠቀም የሰላም ግንባታ ሚናቸውን እንደሚያጠናክሩ በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
በዞኑ የባህላዊ ሽምግልና መማክርት ጉባዔ የምስረታ መድረክ ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሄዷል።
በወቅቱም የዞኑ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፤ የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶችን በመጠቀም የሰላም ግንባታ ሚናችንን እናጠናክራለን ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ቀሲስ ገዛኸኝ ኃይሉ፤ የሀገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀም ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሄ ማበጀት ይገባል ብለዋል።
የመማክርት ጉባዔ መመስረቱም የአብሮነት ባህል እንዲጎለብት በማድረግ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የተጀመሩ ጥረቶችን እንደሚያጠናክር አመልክተዋል።
እንዲሁም ችግሮችን በውይይትና በመመካከር በመፍታት በማህበረሰብ መካከል ያለው መከባበር እንዲጎለብት ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።
የግጭትና የጥላቻን ጎጂነትን በማስገንዘበ አብሮነት እንዲጠናከር እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ ሼህ ኑሩ አባተ ናቸው።
በዚህም መልካም የሆኑ ውጤቶች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ባህላዊ የሽምግልና መማክርት ጉባዔ መመስረቱ ለዘላቂ ሰላም መስፈን የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ሌላው የጉባዔው ተሳታፊ አቶ ዋጋዬ ማሞ በበኩላቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ በመነጋገርና በመመካከር መፍታት ጊዜው የሚጠይቀው ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይም ባህላዊ የችግር አፈታት መንገዶችን በማጠናከር ሰላምን ለማዝለቅ መጠቀም እንደሚገባ አንስተው፤ እርሳቸውም ሚናቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ተዋበች ጌታቸው እንዳሉት፤ አለመግባባቶችን በባህላዊ የችግር አፈታት እውቀቶችን ተጠቅሞ መፍታት ይገባል።
የሰላም መታጣት የቱሪዝም ዘርፉን ጨምሮ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚጎዳ በመሆኑ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የመማክርት ጉባዔው መቋቋም ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ከማስቻሉም በላይ አሁን ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።
በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል እሴቶች ባለሙያ አቶ ደርበው ጥላሁን ሽምግልናን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ የችግር አፈታት ስርዓቶችን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የተቋቋመው ባህላዊ የሽምግልና መማክርት ጉባዔም ትንንሽ ግጭቶችን አሸማግሎ ለችግሮች መፍትሄ በማበጀት አብሮነትንና ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ዛሬ የተቋቋመው የሽምግልና መማክርት ጉባዔ 125 አባላት እንዳሉትም ታውቋል።