ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የእናቶችን የጤና አገልግሎት እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ሰመራ፣ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦በአፋር ክልል የእናቶችን የጤናው ዘርፍ አገልግሎት እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሻሻል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።

ፕሮጀክቱ እናቶችን በገንዘብ መደጎም፤የህጻናት ጤና የተጠበቀና የአመጋገብ ስርዓቱ የተስተካከለ ለማድረግ የተቀረጸ ሲሆን ድጋፉ የተገኘው ከዩኒሴፍ እና ሲዳ ከተሰኙት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች መሆኑም ተመላክቷል።

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ወይዘሮ ነስሮ ኡዳ እንዳሉት፥ ፕሮጀክቱ በክልሉ ኤሊዳአርና ዱለቻ ወረዳዎች የሚገኙ 549 እናቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

በተለይም ከቅድመ እርግዝና ክትትል አንስቶ ከአንድ ዓመት በታች ህጻናትና የሚያጠቡ እናቶችን የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከማድረግም ባሻገር የህጻናት መቀንጨርን መከላከል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ፕሮጀክቱ በወረዳዎቹ የሚገኙ የአርብቶ አደር እናቶች የወሳኝ ኹነቶች አገልግሎትን በተገቢው ለማግኘት የሚረዳቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌሎች ወረዳዎችም መሰል ተግባራት እንዲከናወኑና ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የወረዳዎቹ አመራሮችና ባለድርሻዎች በኀላፊነት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የዱለቻ ወረዳ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ ከሚሴ ሴኮ በበኩላቸው፥ ፕሮጀክቱ በተገቢው ተግባራዊ ከተደረገ የእናቶችን የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በማገዝ ረገድ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ከቅድመ እርግዝናቸው ወቅት ጀምሮ የህክምና ክትትልና የተመጣጠነ ምግብ እንዲያኙ በማድረግ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚረዳ መሆኑን ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ ለ18 ተከታታይ ወራት የሚተገበርም ይሆናል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም