የኩታ ገጠም እርሻ ስነ ዘዴ ምርትና ምርታማነታችንን እያሳደገ ነው -የጨልያ ወረዳ አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኩታ ገጠም እርሻ ስነ ዘዴ ምርትና ምርታማነታችንን እያሳደገ ነው -የጨልያ ወረዳ አርሶ አደሮች
አምቦ፤ ህዳር 3/2018 (ኢዜአ)፡- በኩታ ገጠም የእርሻ ስነ ዘዴ ምርትና ምርታማነታቸውን በመጨመር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን በምዕራብ ሸዋ ዞን የጨልያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
በጨልያ ወረዳ በመኸር አዝመራ በ73 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም የለማን የጤፍ ምርት የወረዳው ኃላፊዎች፣ ሰራተኞችና አርሶ አደሮች ዛሬ ጎብኝተዋል።
በወቅቱ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ወረዳ አርሶ አደሮች እንዳሉት፤ ባለፈት ዓመታት ጤፍን በኩታ ገጠም የእርሻ ስነ ዘዴ በማልማታቸው ምርታማነታቸውን ጨምሮታል።
በልማት ስራው ከተሳተፉ አርሶ አደሮቸ መካከል ታሪኩ ጠኑ እንዳሉት፤ በወረዳው የኩታ ገጠም የእርሻ ተግባራዊ መደረግ ከተጀመረ ወዲህ ምርትና ምርታማነታቸው ጨምሯል።
ቀደም ሲል በልማዳዊ አስተራረስ ጤፍን ያለ ግብርና ባለሙያ እገዛና ያለ ማዳበርያ እንዲሁም ምርጥ ዘርን ሳይጠቀሙ የእርሻ ስራቸውን ያከናውኑ እንደነበር አስታውሰው በዚህም አነስተኛ ምርት ሲያገኙ ቆይተዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የኩታ ገጠም የእርሻ ስነ ዘዴን በመጠቀም ጤፍን በማልማት ምርታማነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ጠቁመዋል።
ጤፍን በክላስተር ተደራጅተው ማምረት ከመጀመራቸው በፊት ከአንድ ሄክታር 10 ኩንታል ምርት ብቻ ያገኙ እንደነበር የገለፁት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ግርማ ድቼ ናቸው።
አሁን ላይ ግን ማዳበርያና ምርጥ ዘር በመጠቀም ምርታማነቸውን ወደ 25 ኩንታል ማሳደግ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህን ልምዳቸውን በመጠቀም በዘንድሮው የመኸር ወቅት ጤፍን በኩታ ገጠም በማልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት ለሰብሉ እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውንም አክለዋል።
የጨልያ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ጪምዲ ረጋሳ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በመኸር እርሻ በወረዳው 26 ሺህ 616 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች የለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 9 ሺህ 636 ሄክታር መሬት በጤፍ የለማ ነው።
አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ጤፍን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን በማልማት ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መሰራቱን አመልክተዋል፡፡
የአሁኑ የመስክ ምልከታም የኩታ ገጠም ጤፍ ልማትን ለማበረታታትና ወደ ስራው ያልገቡ አርሶ አደሮች ልምድ እንዲቀስሙ ለማድረግ ማለሙን አስረድተዋል፡፡
በወረዳው የሰብል ልማትን ለማሳደግ የግብዓት አቅርቦትን ማሳለጥ፣ የባለሙያ ክትትልን ማጠናከርና የሰብል እንክብካቤ ማድረግን የመሳሰሉ ተግባራትን በማከናወን የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አብራርተዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ ቀደም ብለው የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹና የምርት ብክነት እንዳይከሰት ክትትል በማድረግ የሰብል ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑንም አክለዋል።