ቀጥታ፡

በድሬደዋ የመደጋገፍ ባሕልን በማሳደግ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ አበረታች ተግባራት ይጠናከራሉ-ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ፤ሕዳር 3/2018(ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ እርስ በርስ መተባበር እና መደጋገፍ ባሕልን በማሳደግ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ አበረታች ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ከድሬደዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያስገነባቸው 11 ቤቶች ዛሬ ተመርቀው የቁልፍ ርክክብ ተካሂዷል።

ቤቶቹን መርቀው ቁልፉን ለአቅመ ደካማ ወገኖች ያስረከቡት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና ሌሎች አመራሮች ናቸው።

ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ፤ የአስተዳደሩን የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮች ለመፍታት በተለይ በክረምትና በጋው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ በፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ለአቅመ ደካማ ወገኖች የተገነቡት ቤቶች የዚሁ መገለጫ አንዱ ማሳያ መሆናቸውን በመጥቀስ።

እንደ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለፃ፥ የእርስ በርስ መተባበርና መደጋገፍ ባህልን በማሳደግ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ አበረታች ተግባራት በላቀ ደረጃ ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው፥ ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት ወጣቶች ፣ ተቋማትና ባለሃብቶች ጭምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እያደረጉት ያለው ተሳትፎ በአርአያነት የሚጠቀስና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አስገንዝበዋል ።

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እውነቱ ወርቅነህ እንደገለጹት፥ኮርፖሬሽኑ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ ድጋፍ ለሚሹ ቤተሰቦችና ተማሪዎችን ማዕድ በማጋራት፣ የትምህርት መማሪያ ቁሶችን በማመቻቸት የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።

በተለይ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ቤቶች መገንባቱንና ማደሱን ጠቅሰው፤ ይህም ከሳምንት በፊት በቀበሌ ሰባት አራት ቤቶችን ዛሬ ደግሞ በቀበሌ ስምንት አስራ አንድ ቤቶች ማስረከቡን አንስተዋል።

በክረምት የተገኘው ውጤት በበጋ ወራት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ ናቸው።

የቤት ባለቤት የሆኑ ወገኖች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም