ቀጥታ፡

መፍጠር፣ መፍጠን እና በጥራት መሥራት የሁልጊዜም የስራ መመሪያችን ሊሆን ይገባል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦መፍጠር፣ መፍጠን እና በጥራት መሥራት የሁልጊዜም የስራ መመሪያችን ሊሆን ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በሰሜን ሸዋ ዞን በደብረ ብርሃን ከተማ በነበራቸው ቆይታ የመኪና መገጣጠሚያ እንዲሁም የብርጭቆና የጠርሙስ ማምረቻዎችን መመልከታቸውን አስታውቀዋል።



 
በቆይታቸው የተመለከቷቸው ፋብሪካዎች የሀገር ውስጥ ግብዓትን በመጠቀምና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን እያዳኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከብየዳ ጀምሮ ትላልቅ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን እየገጣጠመ የሚገኘው የፊቤላ ኢንዱስትሪያል መኪና መገጣጠሚያ በቀን 12 መኪና ማምረት የሚያስችል አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡ 


 

መገጣጠሚያው በቅርቡ ያስጀመረው አዲስ የቀለም መቀቢያ በርካታ ቀናትን ይወስዱ የነበሩ ስራዎችን በሰዓታት ለማከናወን አስችሏልም ነው ያሉት፡፡

በአንድ ቀን 450 ሺህ ጠርሙስ የሚያመርተው ዴዴ ቦትል የብርጭቆና የጠርሙስ ማምረቻ ደግሞ 86 በመቶ የሚሆነውን ግብዓት ከሀገር ውስጥ ተጠቅሞ ለበርካታ የመጠጥ እና የመድሃኒት ፋብሪካዎች ጥቅም የሚሰጡ ጠርሙሶች እንደሚያመርት አስታውቀዋል፡፡


 

በኢንዱስትሪዎቹ የተመለከትናቸው አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴዎች በየዘርፉ በጥራትና በፍጥነት በመትጋት የምናልመውን እድገት በአጠረ ጊዜ እንደምናሳካ የሚያሳዩ ናቸው ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም