ቀጥታ፡

የትምህርት  ጥራትን ለማረጋገጥ  ለመምህራን ልማትና ግብአት አቅርቦት ትኩረት  ተሰጥቷል

አዳማ ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ  ለመምህራን ልማትና ግብአት አቅርቦት ትኩረት መሰጠቱን የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ገለጹ።

34ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ “ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም” በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።


 

በትምህርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ እሸቱ ገላዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በትምህርት ዘርፉ  ሪፎርም ስራዎች  ለመምህራን ልማትና ፣ ለትምህርት አመራሩ  አቅም ግንባታና ለመጻህፍት ተደራሽነት  ትኩረት ተሰጥቷል።

ሚኒስቴሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ  የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ  ያለሙ  የመማሪያ መጻህፍት ህትመት በማከናወን  ለክልሎች  ማከፋፈሉን  ለአብነት አንስተዋል።


 

በትምህርት ዘርፉ ሪፎርም የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ልማትና ግብአትን ማሟላት ላይም  በትኩረት መሠራቱን ጠቅሰዋል።

በዚህ ረገድ ባለፉት ሁለት የክረምት ወራቶች ልዩ የስልጠና መርሃ ግብር በማዘጋጀት ለ100 ሺህ የሚጠጉ መምህራንና አመራሮች ስልጠና መሰጠቱን አብራርተዋል።

በጉባዔው ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የሲዳማ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በበኩላቸው የትምህርት ዘርፉን ሪፎርም ለማሳካት ሀገራዊና ክልላዊ ሪፎርሞችን በማቀናጀት ተደራሽነትና ጥራትን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።


 

በአገር አቀፉ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ  የተጀመሩ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማስፋት  በገጠር ሞዴል የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን የመገንባትና ነባር የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማደስ ለህጻናቱ  ምቹ  ሁኔታ መፈጠሩን  አብራርተዋል። 

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትምህርት ቤቶቹን ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ ከማድረግ ባለፈ የትምህርት መሣሪያዎችን የማሟላትና የመምህራንን አቅም ማጎልበት ላይ በተጠናከረ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን  በተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር በክልሉ ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ  መቻሉን  ተናግረዋል።

ሌላው የጉባዔው ተሳታፊ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡበከር አዶሽ እንዳሉት ለትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማሳካት  ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተሻለ ስራ ተሰርቷል።


 

የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ኩረጃ ለማስቀረት የሚያስችል ግንዛቤ ከመስጠት ባለፈ  የግብአት አቅርቦትን ማሟላት ላይም በሰፊው መሰራቱን አንስተዋል።  

የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥን  ለማቃለልም  ማህበረሰቡን  በማሳተፍ ከ 30 ሺህ በላይ ህጻናትን ተጠቃሚ ያደረገ  የትምህርት ቤት  ምገባ ፕሮግራሙ  በአስተዳደሩ ተግባራዊ   መደረጉን   ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም