የዘንድሮው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የኢትዮጵያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የፌደሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
በፌደሬሽን ምክር ቤት የመንግስታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገ መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ባንቺይርጋ መለሰ 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበር አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ''ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኀብረብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይከበራል።
ጸሐፊዋ በሰጡት ማብራሪያ ባለፉት አመታት የተከበሩት በዓላት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትሩፋቶች ማስገኘታቸውን ገልጸዋል።
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የኢትዮጵያን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በሚያጠናክሩ ተግባራት እንደሚከበርም አንስተዋል።
በቀኑ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ ህብረ ብሔራዊነት እንዲጎለብትና ፌደራላዊ አስተሳሰብ እና እሴቶችን የሚያሳድጉ ስራዎች እንደሚከናወኑም አመላክተዋል።
በዓሉ ከህዳር 1 ጀምሮ በሁሉም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ሲከበር ቆይቶ ማጠቃለያው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይሆናል ነው ያሉት።
በዚህም ህዳር 25 "የወንድማማችነት ቀን" በሚል የሚከበር ሲሆን እለቱ አብሮነትን የሚያጎለብቱ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
ህዳር 26 "የአብሮነት ቀን" በሚል የሚከበር ሲሆን የብሔር ብሔረሰቦች ልዑካን ሆሳዕና የሚገቡበት ቀን መሆኑን ተናግረዋል።
ህዳር 27 "የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀን" በሚል የሚከበር ሲሆን በእለቱ የክልሉ ጸጋዎች የሚተዋወቁበት መሆኑን አንስተዋል።
ህዳር 28 "የምክክር ቀን" በሚል የሚከበር ሲሆን በፓናል ውይይቶች እንደሚከበር ጠቁመዋል።
ህዳር 29 "የኢትዮጵያውያን ቀን" በሚል ዋናው በዓል የሚከበርበት መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊዋ አመላክተዋል።