ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ተቋማት ላይ ወሳኝ ሪፎርም በማከናወን በኢጋድ ቀጣና ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን ሚናዋን እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በዲሞክራሲ ተቋማት ላይ ወሳኝ ሪፎርም በማከናወን በኢጋድ ቀጣና ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ። 

3ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ ሀገራት ፎረም "ሰላምና ደህንነትን ለማጠናከር የብሔራዊ የዲሞክራሲ ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።  


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢጋድ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።  

ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከራሷ አልፎ በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ማስፈን የሚያስችል ተቋማዊ ሪፎርም ማድረጓን ገልጸዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሰላም ላበረከቱት አስተዋፅኦ የሰላም ኖቤል ሽልማት ማግኘታቸውን ገልጸው፣ በዲሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል። 

ሰላም የዘላቂ ተቋማት ውጤት መሆኑን የገለጹት ቢቂላ (ዶ/ር)፤ የለውጡ መንግስት በጸጥታ አካላት፣ በሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በፍትሕ አካላትና በሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት ላይ ሪፎርም አድርጓል ብለዋል።  

ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ አባል ሀገር የዲሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር መልካም አስተዳደርን በማስፈን ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚና መወጣቷን ገልጸዋል።  

ብዝሀ የዲሞክራሲ ተቋማትን በማሻሻልና አዳዲስ ተቋማትን በመፍጠር ዕውቀት መር የመንግስት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባቱን አንስተዋል። 

ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ስርዓት ማንበር፣ ተጠያቂነት ያለበት የጸጥታና ደህንነት፣ ሙስናን መከላከል የሚያስችሉ ተቋማት ተገንብተዋል ብለዋል። 

ይሄውም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል። 

የኢጋድ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ፤ የኢጋድ ቀጣና እንደ ሽብርተኝነት፣ ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥና በርካታ ፈተናዎች ያሉበት መሆኑን ተናግረዋል።   


 

ዲሞክራሲ ዜጎች በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለፖለቲካ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍ ያለ ዋጋ አለው ብለዋል።      

ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ፣ የሲቪል ማህበራትን ተሳትፎ ማጠናከር አካታች የግጭት አፈታት ስርዓትን ማስፈን እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። 

ምክክርና የሽግግር ፍትህ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበት ወሳኝ መሆናቸውን በማንሳት፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃና የህግ የበላይነትን በማስከበር ገቢራዊ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።  

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ፤ የኢጋድ ቀጣና የጸጥታ ጉዳይ ተለዋዋጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።  


 

በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ለማስፈን መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ እንደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና መሰል የዲሞክራሲ ተቋማትን እያጠናከረች መሆኑን ተናግረዋል። 

ከዚህም ባሻገር በኢጋድ ቀጣና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሀገራት የተቋማት አቅም ማጠናከር እንዳለባችው ታምናለች ብለዋል።  

በቀጣናው የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሰላምና ደህንነት መስፈን እንዳለበት ጠቅሰው፣ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በትብብር መስራቷን አጠናክሮ እንደምትቀጥል ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ ሁለተኛ ጸሀፊ ኤግነስ ጌጀር ፋራህ በበኩላቸው፤ ኢጋድ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የዲሞክራሲ ተቋማትን ሚና ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያዘጋጀው መድረክ ትክክለኛና ወቅታዊ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በኢጋድ ቀጣና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መልካም አስተዳደርን ማንበር ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፣ ስዊድን ለቀጣናው ሰላም በቅርበት ትሰራለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም