ምክር ቤቱ አቶ ጥራቱ በየነን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አድርጎ ሾመ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ አቶ ጥራቱ በየነን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አድርጎ ሾመ
ሀዋሳ ፤ ሕዳር 3/2018 (ኢዜአ)፡- የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አቶ ጥራቱ በየነን የከተማዋ ከንቲባ አድርጎ ሾመ፡፡
ምክር ቤቱ በሁለተኛ ዙር አስረኛ ዓመት የስራ ዘመን ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤው ነው አቶ ጥራቱን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አድርጎ የሾመው።
በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ አቅራቢነት ምክር ቤቱ ሹመቱን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።
የከተማዋ ከንቲባ በመሆን የተሾሙት አቶ ጥራቱ በየነ፤ የሀዋሳ ከተማን የወደፊት ልማት አጠናክሮ በማስቀጠል ለነዋሪዎችና ለእንግዶች ምቹ ለማድረግ መላውን ሕብረተሰብ በማሳተፍ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ከተማዋ ያላትን ሰላም በማፅናት የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል ብሎም የልማት፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የኑሮ ውድነትንና የስራ አጥነት ችግሮችን ለመፍታት እንሰራለን ሲሉም አረጋግጠዋል።