ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል ከ340 ሺህ በላይ ዜጎች  የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ  አከናውነዋል

ጅግጅጋ፤ ህዳር 3/2018 (ኢዜአ)፦  በሶማሌ ክልል ከ340 ሺህ በላይ ዜጎች  የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ማከናወናቸውን የክልሉ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ።

በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የምስራቅ ሪጅን የጅግጅጋ አካባቢ የምዝገባ አስተባባሪ አቶ ጌዲዮን ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለዜጎች ዘርፈ ብዙ አገልግሎትን በተቀላጠፈ መልኩ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ኢትዮጵያ ለያዘችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬታማነትም ቁልፍ ሚናን የሚጫወት ነው ብለዋል።


 

በዚህም በክልሉ የህብረተሰቡን የዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታው ተሳትፎዋቸውን ለማረጋገጥ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን አቶ ጌዲዮን አስታውቀዋል።

በክልሉ ባሉት ዞኖችና በ66 ወረዳዎች በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች፤ በባንኮች፤ በንግድ ማዕከላት እንዲሁም በሌሎች  የመንግሥት ተቋማት ምዝገባው በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ፕሮግራሙ ከተጀመረ ከግንቦት 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን 340 ሺህ ዜጎች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 180 ሺህ የሚሆኑት ከጅግጅጋ ከተማ ውጭ ባሉ ወረዳዎችና ዞኖች የተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በክልሉ እሰከ ሰኔ 2018 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለመመዝገብ መታቀዱን ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ብቻ  ከ160 ሺህ በላይ ዜጎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ የፕሮግራሙን ተደራሽነት በማስፋት ተጨማሪ የምዝገባ ማዕከላት ለመጨመር የሚያስፈልገውን የሰው ሃይል የማሰማራትና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሠቡ ከምዝገባው በኋላ  ከኢትዮ-ቴሌኮምና እውቅና ባላቸው ተቋማት ዲጂታል መታወቂያውን በመውሰድ በጥንቃቄ መጠቀም እንዳለበትም  አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም