ቀጥታ፡

ዜጎች አስከፊነቱን ተገንዝበው መደበኛ ካልሆነ ፍልሰት ሊቆጠቡ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 3/2018(ኢዜአ)፡- በመንግሥት ደረጃ ብሎም ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የሚያከናውነው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ዜጎች ከድርጊቱ እራሳቸውን ማቀብ እንዳለባቸው ተገለጸ።

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና ከፍልሰት ተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈፃሚ ደረጀ ተግይበሉ እንዳሉት፤ መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት ወደ ተለያዩ ሀገራት የሄዱና ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን የመመለስ ሥራ እየተከናወነ ነው።

ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ተገቢው የሥነ-ልቦናና ማኅበራዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጎ ከቤተሰብ እና ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀላቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሎች የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች እና በሥራና ክኅሎት ቢሮዎች አማካኝነት ተገቢውን ስልጠና ወስደው የማቋቋም ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በመንግሥት በኩል ተገቢው ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸው፤ በግላቸው ለመንቀሳቀስ የፈለጉም በራሳቸው ጥሪት የግል ሥራቸውን እየሠሩ መሆኑን አመላክተዋል።

በሀገር ውስጥ ያሉ የሥራ አማራጮችን ማስተዋል እና ወደ ውጭ መሄድ ሲያስፈልግም በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲሆን መክረው፤ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ዘርፈ-ብዙ ጉዳት እንደሚስከትል አስገንዝበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።

ባለፉት አራት ዓመታትም በተለያዩ የመካከለኛ ምሥራቅ፣ የአፍሪካ እና እንደ ማይናማር ያሉ የእስያ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም