ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የሠራተኛውን የዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ለተገልጋዮች ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው

የድሬዳዋ ፤ ህዳር 2/2018 (ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ የሠራተኛውን የዲጂታል ክህሎት በማሳደግ ለተገልጋዮች ቀልጣፋ  አገልግሎት ተደራሽ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የአስተዳደሩ የሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ገለፀ ።

በድሬዳዋ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የመንግስት ሠራተኛውን የቴክኖሎጂ ክህሎት ለማሳደግ በሚቻልበት አግባብ ላይ ቢሮው ከአስተዳደሩ የማዕከል ተቋማት የሰው ሃብት አመራሮች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።


 

ውይይቱን የመሩት የቢሮው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ኢማድ አብዱልቀዩም፤ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የሠራተኞችን የቴክኖሎጂ ክህሎት በማሳደግ የተገልጋዩን ፍላጎት ለማርካት  እየተሰራ ነው።

የሠራተኛውን የቴክኖሎጂ ክህሎት ለማሳደግ ያልተቋረጠ  ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።

ስልጠናውም ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ የመገንባት ጉዞን ለማሳካት ቁልፍ ሚና በመጫወቱ  ሠራተኞች በእድሉ እንዲጠቀሙ  ከተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንተናግረዋል ።

የተሰጠውን ስልጠና በአግባቡ የወሰዱ ሰራተኞች በየተቋማቸው ዲጂታል ቴክኖሎጂን  በመተግበር  ለህዝቡ  ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ እያደረጉ መሆናቸውን  ጠቅሰዋል።

እነዚህን አበረታች ስራዎች በላቀ መጠንና ፍጥነት ለማሳደግ የማዕከል ተቋማት የሰው ሃብት አመራሮች ተግተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል ።

በቀጣይም ተመሳሳይ ውይይት በሁሉም ተቋማት በማካሄድ ሠራተኛው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናው ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ የሰው ሃብት አመራር ዳይሬክተር ወይዘሮ ማሾ መሐመድ በበኩላቸው፤ ሠራተኞች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሠራተኞች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን በአግባቡ በመውሰድ ተገልጋይን ለማርካት በሚደረገው የአሰራር ሂደት ለውጥ  ማምጣት እንደሚገባቸው የገለጹት ደግሞ የአስተዳደሩ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን የሰው ሃብት አመራር ዳይሬክተር ወይዘሮ ፌይሩዝ መሐመድ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም