ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ጂንካ ፤ ሕዳር 2/2018 (ኢዜአ)፡-  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  የወጣቶች  ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ቁጥር ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ወጣቶች ጉዳይና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን  ገለጸ። 

በክልሉ የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች የአቅም ማጎልበቻ የንቅናቄ መድረክ በጂንካ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የክልሉ ወጣቶች ጉዳይና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን  ኮሚሽነር  ማርቆስ ማቲዮስ እንዳሉት ፤ አሻግሮ የሚያይና በሚዛናዊ አስተሳሰብ የተገነባ  ትውልድ ማብዛት ያስፈልጋል። 

አሁን ላይ በክልሉ 512 የስብዕና መገንቢያ ማዕከላት መኖራቸውን ጠቅሰው፤  በቀጣይም የወጣቶች ሁለንተናዊ  ስብዕና መገንቢያ ማዕከላትን ለማበራከት  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶች በሀገራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበትና ልምድ የሚለዋወጡበት አውድም ይመቻቻል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ  የኮሚሽኑ ተጠሪ ተቋማት፣የወጣት ተወካዮችና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች  ተገኝተዋል ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም