መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራሮችን በመቅረፍ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎትን መስጠት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራሮችን በመቅረፍ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎትን መስጠት ያስችላል
ሐረር፤ ህዳር 2/2018 (ኢዜአ)፡- መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራሮችን በመቅረፍ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪና የኢፌዴሪ ፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሰለ በከተማው የተገነባውን የሐረሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ባደረጉት ንግግር በመደመር መንግስት እይታ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሁሉም ዘርፎች እመርታ እያስመዘገብን እንገኛለን ብለዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሰራሮችን በመቅረፍ ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የማዕከሉ ስራ መጀመር በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል ለመስጠት የሚያስችል እና የተገልጋዩን ማህበረሰብ ምልልስና የአገልግሎት ቆይታ ጊዜን የሚያሳጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።
ማዕከሉ በክልሉ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይ ተመጋጋቢ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ለህብረተሰቡ የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ነው የጠቆሙት።
የክልሉ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የጀመረውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
የኢፌዴሪ ፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መሰለ በበኩላቸው በስምንት ክልሎች፣ በሁለት የከተማ አስተዳደሮችና በፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከልን ጨምሮ 18 ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአንድ ቦታ ላይ በክብርና በቅልጥፍና አገልግሎት የሚገኝበትን ስርዓት የያዘና መንግስትና ህዝብን የሚያቀራርብ ትልቅ ስኬት መሆኑንም ተናግረዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች የተሻለ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ የፌዴራልና የክልል ተቋማት አገልግሎቶችን የሚያገኙበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሐረሪ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ ጆርዳን ኢስሃቅ ናቸው።
ማዕከሉ በበቁ ሰዎች የተደራጀና ዘመኑን በሚመጥን አስተሳሰብና በላቀ የስራ ተነሳሽነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ለማገልገል መገንባቱን ገልጸዋል።
በሐረሪ መሶብ አንድ ማዕከል የተለያዩ የፌዴራልና የክልሉ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ከ50 በላይ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ማግኘት ያስችላልም ተብሏል።