የታሪክ ተመራማሪው ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ ፕሮፌሰር በኢትዮጵያ የታሪክ አቀራረብ ሥልት ውስጥ የጋራ ትርክት በመገንባት ዘመን ተሻጋሪ አሻራ አሳርፈዋል - ኢዜአ አማርኛ
የታሪክ ተመራማሪው ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ ፕሮፌሰር በኢትዮጵያ የታሪክ አቀራረብ ሥልት ውስጥ የጋራ ትርክት በመገንባት ዘመን ተሻጋሪ አሻራ አሳርፈዋል
አዲስ አበባ፤ሕዳር 2/2018 (ኢዜአ)፡-የታሪክ ተመራማሪው ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ (ፕ/ር) በኢትዮጵያ የታሪክ አቀራረብ ሥልት ውስጥ የጋራ ትርክት በመገንባት ዘመን ተሻጋሪ አሻራ ማሳረፋቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገለጹ።
የታሪክ ተመራማሪው ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ (ፕ/ር) የአስከሬን ሽኝት ሥነ -ሥርዓት ተካሂዷል።
በሽኝት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር)፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣የሀይማኖት አባቶችን ጨምሮ የፕሮፌሰሩ የሥራ ባልደረቦችና ወዳጅ ዘመዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ (ፕ/ር) በኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የጋራ ትርክትን ለመገንባት የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸው ተገልጿል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ፕሮፌሰር ላጲሶ በአካታች የታሪክ አዘጋገብ በአካዳሚው ዘርፍ ብርቱ ትጋት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የተዛባ የታሪክ ገጽን በማረቅ የጋራ ትርክት መገንባት ላይ አሻራቸውን ማሳረፋቸውንም ነው የገለጹት።
ፕሮፌሰሩ ከሀገራቸው ባለፈ በጥቁር አፍሪካውያን የታሪክ ምልከታ ላይ አስተዋጽኦ ነበራቸው ብለዋል።
የጋራ ትርክትን ለመገንባት ያደረጉት ጥረት ሀገር ወዳድነታቸውን ያሳያል ብለዋል።
ቢጻፍም ባይጻፍም ሁሉም የራሱ ታሪክ አለው በሚል አቋማቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰሩ፤ በኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ጥልቅ ጥናትና ምርምር ማድረጋቸውም ተናግረዋል።