በክልሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል- ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል- ምክር ቤቱ
ባሕርዳር ፤ሕዳር 2/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ማክበር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ምክር ቤት አስታወቀ።
የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ማለፉ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በዓሉ በየዓመቱ ሁሉም ክልሎች በአንድ ላይ በመሰባሰብ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያከብሩት እንደቆዩ አውስተዋል።
ይህም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ትስስር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ፣ በመተማመንና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ አንድነት እየጎለበተ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።
በዚህም የተገኘውን ውጤት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ክልሉ የድርሻውን ሲወጣ እንደቆዩ አመልክተው፤ የዘንድሮውም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሕዳር ወር በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር በዐቢይ ኮሚቴ የሚመራ ስድስት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ስራ ጀምረዋል ብለዋል።
ዓላማውም በዓሉ ሲከበር በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳብር በማድረግ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ ለማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል።
በዓሉ የፌደራሊዝምና የሕገ መንግስት አስተምህሮዎችን በማጠናከር የክልሉና የሀገሪቱን ገጽታ በመገንባት ላይ በማተኮር እንደሚከበር ተናግረዋል።
በዚህም በወሩ ያሉ አራት ሳምንታትን የአስተምሮ ሳምንት፣ የበጎ ፈቃድ፣ የሕብረብሔራዊ አንድነትና ግንኙነት ማጠናከሪያና የማጠቃለያ ሳምንት በሚል ከእነዚህ ስያሜዎች ጋር የተያያዙ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
የዘንድሮውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በክልሉ ሕዳር 5/2018 ዓ.ም በይፋ የሚጀመር ሲሆን፤ ሕዳር 24 የማጠናቀቂያ መረሃ ግብር እንደሚካሄድ በመግለጫው ተመላክቷል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ለሚከበረው በዓልም ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ የባሕል ቡድን አባላትና ሌሎችም እንግዶች እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል።