ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የሴቶችን የገቢ አቅም ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አምቦ፣ህዳር 2/2018(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል የሴቶችን የገቢ አቅም ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ  ገለፀ።

የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀሬ ወረዳ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞች የተገነቡ መኖሪያ ቤቶችን አስረክቧል።

በዚሁ ጊዜ የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

በተለይም አቅም የሌላቸው እና የቤተሰብ ሀላፊ የሆኑ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማሳደግ እንዲችሉ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

ባለፈው የክረምት ወራት የተጀመሩ የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ በዚህ ወቅት ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች እየተላለፈ መሆኑን ጠቅሰው ቀሪዎቹንም አጠናቆ ለማስረከብ የሚደረገው ርብርብ ይቀጥላል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ሴቶች በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም በርካታ ሴቶች በወተት ላም እርባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዶሮ እርባታ እና በሌሎች የስራ ዘርፎች ተሰማርተዋል ብለዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ሰቶችና ህፃናትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ክብቱ ድሪባ በበኩላቸው፣ በዞኑ የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር  በመተባበር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በክረምት ወራት የተጀመሩ የአቅመ ዳካማ ሴቶች ቤት ግንባታ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች እየተሰጠ መሆኑን ተናግረው በትናንትናው እለትም ሁለት መኖሪያ ቤቶች መተላለፋቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በኤጀሬ ወረዳ አቅመ ደካማ ሴቶች ተደራጅተው በወተት ላሞች እርባታ መሰማራታቸውን ገልጸው ተጠቃሚነታቸውም እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል።


 

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መኖሪያ ቤት የተገነባላቸው ወይዘሮ ብርቄ ዳባ፣ የገንዘብ አቅም ስለሌላቸው ሊፈርስ የተቃረበ ቤት ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ እንደነበረ አስታውሰዋል።

አሁን  በተገነባላቸው አዲስ መኖሪያ ቤት ችግራቸው የሚቀርፍላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው በጎ ፈቃደኞችንም አመስግነዋል።


 

በሌላ በኩል በማህበር ተደራጅተው ስራ ከጀመሩ ሴቶች መካከል ወይዘሮ ባይሴ ቱሉ እንዳሉት፣ በተሰማሩበት የወተት ላም እርባታ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚተጉ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም