ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምታቅደውን ብልጽግና እውን ማድረግ የሚችሉ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቷል

አዳማ፤ህዳር 2/2018( ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የምታቅደውን ብልጽግና እውን ማድረግ የሚችሉ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት ለትምህርት ጥራት ትኩረት መሰጠቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

34ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ “ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም” በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባዔው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የትምህርት ዘርፉ ውጤታማ ዜጎችን ማፍራት እንዲችል መግባባት ተፈጥሮ ጥራትን ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በትምህርት ዘርፉ ያሉትን ማነቆዎች በመፍታት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ የምታቅደውን ብልጽግና እውን ማድረግ የሚችሉ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቶ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጉባዔውም በትምህርት ዘርፉ ታቅደው የተሰሩ ስራዎችን በጋራ ለመገምገምና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።

በጉባዔው የትምህርት ሴክተሩን ለማሳካት የተያዙ ግቦች ዙሪያ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የጠራ አመለካከት በመያዝ ይበልጥ መረባረብ እንደሚገባቸው ለማስገንዘብ መሆኑን አንስተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በክልሉ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ትኩረት በመስጠት ለትምህርት ጥራት መሰረት መጣሉን አንስተዋል።

የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ እና ሌሎችንም ችግሮች ለመፍታት ሁላችንም በሚገባን ልክ ተሰናስለን የትምህርት ሥርዓቱን መምራት ይኖርብናል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በጉባዔው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣የክልል ትምህርት ቢሮ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ እና አጋር አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም