ቀጥታ፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሮግራሞች ክለሳ በዚህ ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ በገቡ ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል

አዲስ አበባ፤ሕዳር 2/2018 (ኢዜአ)፡-የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሮግራሞች ክለሳ በዚህ ዓመት ወደ ዩኒቨርስቲ በሚገቡ ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በ2018ዓ.ም አዳዲስ ከ80 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራሞች እንደሚከለሱ ተመላክቷል፡፡

‎የትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ መንግስት የትምህርት ጥራትን እና አግባብነት ለማረጋገጥ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል የከፍተኛ ስርዓተ ትምህርት ፕሮግራሞች ክለሳ ይገኝበታል።

‎የፕሮግራሞች ክለሳ ዓለም አቀፍ የትምህርት ስታንዳርዶችን የጠበቀ የትምህርት ጥራት አግባብነትን በማረጋገጥ የሀገሪቱን የልማት አቅጣጫዎች የሚደግፍ መሆኑን አንስተዋል። 

‎ቀደም ሲል የነበረው ሥርዓተ ትምህርት በንድፈ ሀሳብ ላይ ያተኮረ መሆኑን የተናገሩት መሪ ስራ አስፈጻሚው፤ አሁን ያለው ክለሳ ግን ተማሪዎች ተወዳዳሪ የሚያደርግ ተግባር ተኮር እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።

‎የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራሞች ክለሳ በዘመናዊው ዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ የሚፈለጉትን ክህሎቶች፣ ችግር ፈቺነት፣ ፈጠራ፣ እና ሙያዊ ስነምግባርን ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል። 

‎ክለሳው የሀገር በቀል እውቀትን በማካተት የትምህርት ተቋማቱን ልዩ ከማድረጉም በላይ ተመራቂዎች በየትኛውም የዓለም ክፍል እንዲማሩና እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።

መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) በሀገረቱ በመጀመሪያ ዲግሪ 314 ፕሮግራሞቸ መኖራቸውን አንስተው፤  በቀጣይ ሁሉም የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ ክለሳ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

እስካሁን አምሳ አምስት ፕሮግራሞች መከለሳቸውን ጠቁመው፤ 2018ዓም ሰማንያ አዳዲስ ፕሮግራሞችን በመከለስ በአጠቃላይ ከ100 በላይ ለማድረስ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

‎ሚኒስቴሩ የትምህርት ፕሮግራሞቹ ክለሳ ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ ክለሳው  ወደ ስራ ሲገባ መምህራን አዲሱን ይዘትና የአተገባበር ዘዴ ለመረዳት የሚያስችላቸው ሙያዊ ሥልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሮግራሙ ክለሳ በዚህ ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ በገቡ ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆኑ በመሰረታዊነት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በኩል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡ 

‎የክለሳው ዓላማ ውጤታማ እንዲሆን የዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም