በምርምር የወጡ የስንዴ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ ለስንዴ ምርታማነት ትኩረት ተሰጥቷል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
በምርምር የወጡ የስንዴ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ ለስንዴ ምርታማነት ትኩረት ተሰጥቷል - ሚኒስቴሩ
ሰመራ፤ ጥቅምት 22/2018(ኢዜአ)፦ በምርምር የወጡ የስንዴ ዝርያዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በማስተዋወቅ ለስንዴ ምርትና ምርታማነት ትኩረት መሰጠቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት አማካኝነት ለግብርና ባለሙያዎች የተዘጋጀ ስልጠና ዛሬ በሰማራ ከተማ ተሰጥቷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የፕሮጀክቱ ብሔራዊ አስተባባሪ አብዱሰመድ አብዱ እንዳሉት፣ ፕሮጀክቱ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና አለው።
ስንዴ ለአብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል የምግብ ሉአላዊነቱን የሚያረጋግጥ ሰብል በመሆኑ ከስንዴ ልማት አርሶ አደሩ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች ባሉ 76 ወረዳዎች ላይ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው፤ በአፋር ክልል አፋምቦ፣ አሚበራና ዱብቲ ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
እስካሁንም በዱብቲ ወረዳ በሰፋፊ መሬቶች ላይ ውስን ጉልበት በመጠቀም የሜካናይዜሽን እርሻ ለማከናወን የቦታ ልየታ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ በአፋር ክልል በተመረጡ አካባቢዎች በምርምር የወጡ የስንዴ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ የማድረስ ሥራ እንደሚከናውን ገልፀው፣ ከስንዴ በተጨማሪ ለአኩሪ አተርና ለሩዝ ዝርያዎች ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል።
በአፋር ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር ሃመዱ መሐመድ በክልሉ በአዋሽ ወንዝ ተፋሰሰ ላይ በሚገኙ 11 ወረዳዎች የስንዴ ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የመስኖ ውሃን በመጠቀም በክልሉ የስንዴ ልማት በባለሃብቶች፣ በከፊል አርብቶ አደሮችና በማህበራት አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።
የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ የአፋር ምርጥ ዘር ኢንተርኘራይዝ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት እንዳሉ ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ በስንዴ ልማት ላይ ምርታማነትን ለማሳደግ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ገልፀዋል።